በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ የታገቱት ስድስት ታዳጊዎች ለምን ተገደሉ?

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ የታገቱት ስድስት ታዳጊዎች ለምን ተገደሉ?

(bbcamharic)—ከጠገዴ ወረዳ ታግተው ከተወሰዱ ስምንት ታዳጊዎች መካከል ስድስቱ መገደላቸውን የጠገዴ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ እሸቴ አረጋዊ ለቢቢሲ አረጋገጡ።

ታዳጊዎቹ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የተወሰዱት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ ማይዳራ በሚባል ወንዝ አካባቢ ከብት በመጠበቅ ላይ ሳሉ እንደነበረ አቶ እሸቴ ይናገራሉ።

እድሜያቸው ከ10-16 የሚሆኑት ታዳጊዎች፤ ከተያዙ በኋላ አጎራባች ወደሆነው ታች አርማጭሆ ወረዳ ተወስደዋል።

ታዳጊዎቹ በታች አርማጭሆ ለ9 ተከታታይ ቀናት ታግተው ከቆዩ በኋላ፤ ታህሳስ 19 በጥንድ ታስረው ከስምንቱ ስድስቱ በጥይት ተመተው ተገድለዋል።

ከሟች ታዳጊዎቹ መካከል አንደኛው ቤተሰቡን ለመርዳት ሰው ቤት በእረኝነት ተቀጥሮ የሚሰራ ነበር።

በሕይወት ከተረፉት ታዳጊዎቹ አንዱ በጥይት ቆስሎ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ወደ ገደል በመንከባለሉ ከአጋቾቹ ማምለጥ ችሏል።

መረጃውን ለሚመለከተው አካል የተናገረውም ይሄው ወደ ገደል ተንከባሎ ያመለጠው ታዳጊ መሆኑን አቶ እሸቴ ገልፀውልናል።

የጠገዴ እና ታች አርማጭሆ ወረዳ የፀጥታ አካላት የታዳጊዎቹ መጥፋት ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ፍለጋ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አቶ እሸቴ ያስታውሳሉ።

ልጆቹ የተወሰዱት ከጠገዴ ወረዳ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሉ ትኩረትም እዚያው አካባቢ ላይ ስለነበር የፀጥታ አካላት በወረዳው ያሉ ቀበሌዎች ሲያስሱ ነበር የቆዩት።

“ቦታው ዘወር ያለ ነበር፤ ኮከራ ቀበሌ የሚባል ድሮም ‘የሽፍታ መጠጊያ’ ይባላል። እዚያ ወስደው ነው የገደሏቸው” ይላሉ አቶ እሸቴ።

በመጨረሻም የመገደላቸውን መረጃ የሰሙት፤ ጓደኞቹ ሲገደሉ ወደ ገደል ተንከባሎ በመውደቁ ከግድያው ከተረፈው ታዳጊ ነው። በታዳጊው ላይ ተኩስ ቢከፍቱበትም ማምለጥ በመቻሉ ለፀጥታ ኃይሉ ጥቆማ ሰጥቷል።

አቶ እሸቴ ከሞት ከተረፈው ታዳጊ አገኘሁት ያሉትን መረጃ አጣቅሰው፤ ግለሰቦቹ ታዳጊዎቹን ያገቷቸው ወደ ወላጆቻቸው ስልክ እየደወሉ ገንዘብ አምጡ እያሉ በማስፈራራት ገንዘብ ለመቀበል አልመው ነበር።

አጋቾቹ አንድ ታዳጊን ለመልቀቅ ከ100 ሺህ ብር በላይ ጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ በድርድር 50 ሺህ ድረስ ወርደው እንደነበር መስማታቸውን ኃላፊው ይናገራሉ።

በአጠቃላይ ወላጆች ለስምንቱ ህፃናት ከ500 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር።

ወላጆች ድምጻቸውን ለመንግሥት አካል ከማሰማት በቀር የተጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው ልጆቻቸው ተገድለዋል።

የ6ቱ ሕፃናት አስክሬን ከሞት ያመለጠው ታዳጊ በሰጠው ጥቆማ መሠረት፤ በፀጥታ አካሉና በማህበረሰቡ ትብብር አስክሬናቸው ከሥፍራው እንዲነሳ የተደረገ ሲሆን፤ ዛሬ በጠገዴ ገብርዔል ቀበሌ፣ ገብርዔል ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈፅሟል።

ግድያውን የፈሙትን ግለሰቦች በተመለከተ የጠየቅናቸው አቶ እሸቴ፤ “የወረዳው አሊያም የታች አርማጭሆ ሽፍታ ይባላል፤ እስካሁን ግን እገሌ ተብሎ የታወቀ ነገር የለም፤ እየተጣራ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ተጠርጣሪዎቹን አድኖ ለመያዝ ፍለጋ ላይ እንዳለም አክለዋል።


ተደጋጋሚ እየሆነ የመጣው እገታ
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር በሚገኙ ሥፍራዎች ውስጥ በተደጋጋሚ ስለሚታገቱ ሰዎች ዜና መስማት የተለመደ ይመስላል።

ለዚሁ የእገታ ወንጀል በብዛት ሰለባ ከሚሆኑት መካከል ደግሞ አሽከርካሪዎች ይገኙበታል።

አህመድ ይማም የአይሱዙ የጭነት መኪና አሽከርካሪ ነው። አህመድ ከመተማ-ሽንፋ-ፎገራ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሸቀጣ ሸቀጥና ሰሊጥ ያመላልስ እንደነበር ይናገራል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከመተማ ተነስቶ ወደ ፎገራ ሸቀጣ ሸቀጥና ሰው ጭኖ ሲጓዝ ስድስት ታጣቂዎች መኪናውን በማስቆም እሱን፣ ረዳቱንና ሁለት ተሳፋሪዎች ሽንፋ ቀበሌ ላይ ማገታቸውን ይናገራል።

አህመድ በታጣቂዎቹ እጅ ሦስት ቀን መቆየቱን የተናገረ ሲሆን፤ ታጣቂዎቹ እንደታገተ የወሰዱት አሞሃ ተራራ ወደሚባል ከፍ ያለ ተራራማ ሥፍራ ላይ መሆኑን ያስታውሳል።

አህመድ እንደሚለው እነሱ ከታገቱበት ሥፍራ በሁለት ሰዓት የእግር መንገድ ርቀት ላይ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ቢኖርም ማንም የደረሰላቸው እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጿል።

ከዚያም መታገታቸውን ለቤተሰቦቹና ጓደኞቹ መናገሩን ይናገራል።

ታጣቂዎቹ እገታውን የፈፀሙት ከንጋቱ 12 ሰዓት ገደማ መሆኑን የሚናገረው አህመድ፤ ወደ ተራራው ከወሰዷቸው በኋላ ሌሎች ሦስት ያልታጠቁ ባልደረቦቻቸውን መመልከቱን ይገልጻል።

መንገድ ላይ እንዳስቆሟቸው መኪናውንና እነርሱን መፈተሻቸውን ይሁን እንጂ በቂ ገንዘብ አለማግኘታቸውን ተናግረው ወደ ተራራው ከወሰዷቸው በኋላ በነፍስ ወከፍ ሦስት መቶ ሺህ ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ይናገራል።

ከብዙ ልመና እና ድርድር በኋላ 120 ሺህ ብር ከፍሎ መለቀቁን ገልጿል።

ድርድሩ ሲካሄድ የነበረው እና ገንዘቡን የሰጣችሁት በምን ሁኔታ ነው ተብሎ ሲጠየቅ፤ “ከቤተሰቦቻችን ጋር ለመነጋገር ሞባይል ኔት ወርክ ወዳለበት አካባቢ ይዘውን ይሄዳሉ” ብሏል። የከፈለውን ገንዘብም ወንድሙ ጫካ ድረስ በመሄድ በጥሬ ገንዘብ መክፈሉን ያስረዳል።

“ፖሊስ ወይንም ሌላ ሰው ይዞ ቢመጣ እንደሚገሉኝ ስለነገሩት፤ ብቻውን ጫካ ድረስ መጥቶ ከእነርሱ ለአንዱ ከፍሏል” ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

አህመድ ለረዳቱ 15ሺህ ለአንዱ ተሳፋሪ ደግሞ 70ሺህ ብር መከፈሉንና መለቀቃቸውን እንደሚያስታውስ ጨምሮ አስረድቷል።

በእስር ላይ በቆዩበት ወቅት ትንሽ ቆሎና አንድ ኩባያ ውሃ እየተሰጣቸው መቆየታቸውን በመናገር፤ ከእርሱ ሌላ 250ሺህ ብር ከፍለው የወጡ፣ ከሽንፋ ማዶ ቋራ የሚባል አካባቢ ደግሞ ታግተው ከነበሩ 10 ሰዎች፤ ሁለቱ ከሁለት ቀን በፊት 400 ሺህ ብር ከፍለው መውጣታቸውን እንደሚያውቅ ነግሮናል።


በሕፃናት ላይ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሲፈፀም በአካባቢው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያሉት የጠገዴ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ እሸቴ አረጋዊ፤ በሌሎች አዋቂዎች ላይ ግን “ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች” ሲሉ በገለጿቸው ግለሰቦች ገንዘብ አምጡ እየተባሉ መታገታቸው አዲስ ነገር አይደለም ብለዋል።

“ግድያው የመጀመሪያ ቢሆንም፤ አግቶ ገንዘብ መቀበሉ ግን አዲስ ክስተት አይደለም” በማለትም ከዚህ ቀደም እገታ በመፈፀም ገንዘብ የሚጠይቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው እስከ 25 ዓመት እስር የተፈረደባቸው እንዳሉም ያስታውሳሉ።

አቶ እሸቴ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ሥር ውለው የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባው ወንጀለኞች ‘ሽፋታ’ በመሆን በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታወቁ ናቸው ብለዋል።

በአካባቢው የተለየ የፀጥታ ቁጥጥር ይደረጋል የሚሉት አቶ እሸቴ፤ መከላከያ፣ ልዩ ኃይል እና የቀበሌ ሚሊሻ ወደ በርሃ ድረስ በመግባት በየቀበሌው ተሰማርቶ እንደሚገኝ ገፀውልናል።

በተመሳሳይ ከአንድ ሳምንት በፊት ከቋራ ወደ ጎንደር ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ነፍስ ገበያ ተብላ በምተጠራ አካባቢ ማንነታቸው በማይታወቅ ሰዎች ታገቶ ስድስት ሰዎች መወሰዳቸው ተነግሮ ነበር።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ ለአካባቢው አስተዳደር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ለጊዜው ምርመራ ላይ ነን በሚል ምክንያት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።