በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተጨማሪ ስድስት የመንግሥት ኃላፊዎችና

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተጨማሪ ስድስት የመንግሥት ኃላፊዎችና አንድ ባለሀብት ፍርድ ቤት ቀረቡ
 የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር 45 ደርሷል

(Ethiopian reporter) —መንግሥት ከሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤት ካቀረባቸው 38 የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በተጨማሪ፣ ስድስት የመንግሥት ኃላፊዎችና አንድ ባለሀብት ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ የተጠርጣሪዎቹም ቁጥር ወደ 45 አሻቅቧል፡፡

በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው የመንግሥት ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የቤቶች ልማት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ ሽመልስ አለማየሁ፣ የመሬት ዝግጅትና መሠረተ ልማት ዲዛይን ረዳት ኃላፊ ወ/ሮ ሳባ መኮንን፣ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዘነበ ይማም፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የኤሌክትሪክ መሐንዲሶች ቡድን መሪ አቶ አስናቀ ምሕረትና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዕቃ አቅርቦትና ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተስፋዬ ተድላ ናቸው፡፡ ባለሀብቱ ደግሞ ቀደም ብሎ ፍርድ ቤት ቀርበው ከነበሩት ተጠርጣሪዎች ጋር ቀርበው የነበሩት አቶ የማነ ግርማይ ናቸው፡፡

ሦስቱ ከቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ከሰባት ዓመታት በፊት በተካሄደ የመንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከባለሀብቱ አቶ የማነ ግርማይ ጋር በመመሳጠር፣ ውል ሳይደረግ በተደረገ የኮንክሪት ሙሌትና ሌሎች ሥራዎች ደረጃውን ያልጠበቀ ሥራ መከናወኑን እያወቁ፣ የ39,727,693 ብር ጉዳት በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ማድረሳቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የቀድሞ የመተሐራ ስኳር ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዘነበ ደግሞ ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸውና የህንድ ኩባንያ ከሆነው ስታር ኃላፊነቱ ተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በመመሳጠር፣ 1,164,465 ዶላር ክፍያ ፈጽመው ጉዳት በማድረሳቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

የፋብሪካው የዕቃ አቅርቦትና ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ፣ በ2004 ዓ.ም. ለፋብሪካው ግንባታ ለቀረበው የአርማታ ብረትና ሲሚንቶ፣ ከህንድ ኩባንያ ስታር ጋር በመመሳጠራቸው ክፍያ ተቀንሶ በዓይነት መመለስ ሲገባው ሳይመለስ በመቅረቱ፣ 31,330,375 ብር ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውን ቡድኑ አስረድቷል፡፡ 221,375 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው የታሰሩት የፋብሪካው ኤሌክትሪክ መሐንዲሶች ቡድን መሪ አቶ አስናቀ ሲሆኑ፣ ጉዳቱን ያደረሱት ከታዘዘው የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚመጣጠን ጄኔሬተር ውጪ በማቅረብ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ የተገኘው ጉዳት መነሻ በመሆኑ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ቡድኑ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣዎቹ በመጀመሪያ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት መቃወሚያ፣ 14 ቀናት መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ነው፡፡ ማስረጃ ከተሰበሰበ በኋላ እንደተያዙ መገለጹን ያስታወሱት ተጠርጣዎቹ፣ እነሱም የተያዙት ሕጉን በጠበቀ መንገድ ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ ከሰበሰበ በኋላ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ግን ዋስትናውን እንደሚቃወም አሳስቦ በሰጠው ምላሽ እንደተናገረው፣ ሥራው ገና ጅምር እንጂ ምንም ያልተነካ በመሆኑ በዋስትና ቢወጡ ማስረጃና ምስክር ሊያሸሹና ሊደብቁ ስለሚችሉ፣ የዋስትናው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ተከራካሪ ወገኖች ካዳመጠ በኋላ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጄክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ላይ የተጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ፣ ለነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ኃላፊዎችና ባለሀብቱ የተጠረጠሩበት ቀደም ብሎ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከነበረው ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመጠቆም፣ ዘጠኝ ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበበት የዶ/ር መረራ አቤቱታ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ

የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን መከልከሉን የተቃወሙት መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ጉዳያቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ስለሚያስፈልገው የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ እንዲጠjቁ ተነገራቸው፡፡ ውሳኔውን የሚሰሙት በሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡

ሦስት የተለያዩ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱባቸው ዶ/ር መረራ በክሶቹ የተጠቀሱባቸው የሕግ አንቀጾች የምስክሮችና የማስረጃ ዝርዝሮች እንዳይደርሳቸው የማይከለክሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/01 አንቀጽ 32ን በመጥቀስ እንዳይሰጣቸው መከልከሉን ተቃውመው ነበር፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ፣ ለ፣ 38(1)፣ 27(1)፣ 238(1) እና (2)ን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 12(1)፣ 2(1) የወንጀል ሕግ 486(ለ) ማለትም በጋራ በመተባበር፣ ወንጀል ለማድረግ በማደም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ወንጀል ለማድረግ በመስማማት፣ የሐሰት ወሬ በማውራትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመጣስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ሳለ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32 በመጥቀስ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይሰጣቸው መከልከሉ ተገቢ ያልሆነና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀረበለትን የመቃወሚያ አቤቱታ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም?›› በማለት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባዔ የላከው ቢሆንም፣ ውሳኔው ሊደርስ ባለመቻሉ ለቀጣይ ዓመት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የምስክሮች ዝርዝር ‹‹ለተከሳሽ ሊሰጥ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱት በዶ/ር መረራ ክስ ብቻ አለመሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ በርካታ የክስ መዝገቦች ላይ ጉዳዩ በመነሳቱ ቀደም ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ምክር ቤቱ ግን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መላኩን ከመግለጽ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ ውሳኔውን መጠበቅ የግድ እንደሚል አስረድቷል፡፡

የዶ/ር መረራ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዶ/ር መረራ ከታሰሩ ዘጠኝ ወራት ሞልተዋቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የዓመቱን ሥራ ሊያጠናቅቅ የቀረው ከ15 ቀናት አይበልጥም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በራሱ የመተርጎም ሥልጣን ስላለው ተርጉሞ ወይም የምክር ቤቱ ውሳኔ የሚፈጥንበት ሁኔታ ካለ ተባብሯቸው፣ ወደሚቀጥለው ዓመት ከመተላለፉ በፊት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ዶ/ር መረራ በክርክር መቃወሚያቸው ምክንያት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን አስታውሶ፣ የመቃወሚያ ሐሳባቸውን ለማንሳት ፈልገው ከሆነ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ የዶ/ር መረራ ጠበቆች ተመካክረው ምላሽ ሲሰጡ መቃወሚያ ያቀረቡት ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሆኑን በመጠቆምና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ እንደሰጠበት ተናግረው፣ መቃወሚያቸውን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ዶ/ር መረራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንኳን ሳይሰጡ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መቃወሚያችሁን አንሱ የሚል ጥያቄ አለማቅረቡን ገልጾ፣ እሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት መቃወሚያቸውን እያነሱ ስለመሆናቸው ለማወቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌላ ተከሳሽ እንዲመላለስና እንዲጉላላ ፍላጎት እንደሌለው በመንገር፣ መዝገቦችን የሚያስተናግደው ክስ በተመሠረተበት ጊዜ (ዕድሜ) ቅደም ተከተል ከመሆኑ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ መጠበቁ ለተከሳሹም ሆነ ለፍርድ ቤቱ ጥቅም ስላለው፣ ለጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. መሸጋገሩ የግድ መሆኑን በማስረዳት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የዶ/ር መረራ ጠበቃ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ የጥብቅና ፈቃድና ውክልና እያላቸው ማረሚያ ቤት ደንበኛቸውን እንዳይጎበኙና እንዳያነጋግሩ እንደከለከላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲያገናኛቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ታምሩ ጽጌ

Exit mobile version