ቁርጡ ያልታወቀው የታሳሪ ቤተሰቦች ጥበቃ

ርጡ ያልታወቀው የታሳሪ ቤተሰቦች ጥበቃ

(bbcamharicnews)—ዕለተ ረቡዕ ታህሳስ 25/2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽህፈት ቤት “ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ በአቃቢ ሕግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙና የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ሕግና ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ እንዲፈቱ ተወስኗል” ሲል መግለጫ ያወጣው።

መግለጫው ከወጣበት ዕለት ጀምሮ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰለቸን ሳይሉ በተለይ ደግሞ ቂሊንጦ፣ ዝዋይ እና ማዕከላዊ እስር ቤቶች አቅራቢያ እየዋሉ በር በሩን እያዩ ነው።

አመፅና አድማ በማስነሳት ወንጀል ተፈርዶበት እስር ላይ የሚገኘው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዮናታን ተስፋዬ ቤተሰብ ዜናው ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ መፈታቱን እየጠበቁ ነው።

“ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ልጃችን ሊለቀቅ ይችላል ብለን በጉጉት ስንጠብቅ ብንቆይም እስካሁን ምንም ዓይነት ፍንጭ የለም” ይላሉ ልጃቸው ዮናታን ተስፋዬ በዝዋይ እስር ቤት የሚገኘው፤ አቶ ተስፋዬ ረጋሳ።

በፍርድ ሂደት ላይ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ልጅ ቦንቱ በቀለ ግን ውሳኔው ተግባራዊ ሆኖ ካላየች ለማመን እንደምትቸገር ትናገራለች።

“መንግሥት ጠዋት የተናገረውን ከሰዓት ስለማይደግመው ከእስር ወጥቶ እንደ ቀድሞው አብረን ቁርስ ስንበላ ብቻ ነው የማምነው” ትላለች።

የዮናታን አባት የመንግሥት ውሳኔ ከተሰማ በኋላ ልጃቸውን ባያገኙትም ሌሎች ወዳጅ ዘመዶቹ ሄደው ጎብኝተውታል። ”ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በመግለጫው መሠረት እኔም ከእስር ልለቀቅ እችላለሁ ብሎ እየጠበቀ እንደሆነም አጫውቷቸዋል” ይላሉ አቶ ተስፋዬ።

ቢቢሲ ይህንን ዜና በሚያሰናዳበት ወቅት አቶ በቀለ ገርባ ለሕክምና እርዳታ ከእስር ቤት ውጭ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

ልጃቸው ቦንቱ ለቢቢሲ እንደተናገረችው “እኔስ ለምጄዋለሁ፤ ታናናሽ ወንድሞቼ ግን ትምህርታቸውን መከታተል ተስኗቸዋል” ትላለች።

በነበቀለ ገርባ የክስ መዝገብ ውስጥ የሚካተቱት የኦፌኮ አባላቱ አዲሱ ቡላላ እና ደጀኔ ጣፋ መግለጫውን በተመለከተ እስካሁን ምንም ዓይነት ነገር እንዳልሰሙ እንደነገሯትም ገልፃለች።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ መሠረት ከእስረኞች መፈታት በተጨማሪ የተለያዩ ሰቆቃዎች በእስረኞች ላይ እንደሚፈፀምበት ሲነገር የቆው ማእከላዊ የምርመራ ማእከል እንዲዘጋ ተወስኗል ብለዋል።

‘አምነስቲ ኢንተርናሽናል’ የተሰኘው የመብት ተሟጋች ቡድን የእስረኞች መፈታትና የማዕከላዊ መዘጋት ዜና እንደተሰማ ”የአስከፊው የጭቆና ዘመን ማብቃት ምልክት ሊሆን ይችላል” ብሎ እንደዘገበ አይዘነጋም።

ነገር ግን ከመንግሥት በኩል ስለሂደቱም ሆነ የትኞቹ ግለሰቦች ከእስር ሊለቀቁ እንደሚችሉ የተሰጠ ፍንጭ የለም።

“ምንም እንኳ በይግባኙ መሠረት የዮናታን የእስር ጊዜ ከስድስት ዓመት ተኩል ወደ ሦስት ዓመት ተኩል ቢቀነስም ሙሉ በሙሉ ከእስር ተለቆ ደግሞ ብናዬው ቤተሰቡና ወዳጅ ዘመዶቹ ከምንም በላይ ደስተኛ ልንሆን እንደምንችል ጥርጥር የለውም” ይላሉ አቶ ተስፋዬ።

አክለውም “መግለጫው ከድርጊቱ በፊት መጥቶ የእኛን ቤተሰብም ሆነ ሌሎች ወዳጅ ዘመዶቻቸው በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን አጉል ጉጉት ላይ ከሚጥል ተግባሩ ቢቀድም የተሻለ ነበር” በማለት ውሳኔውን ተከትሎ የተከሰተውን ጉጉት ይጠቅሳሉ።

ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር ካለ በሚል ፌዴራል ማረሚያ ቤትን ጠይቀን “እስካሁን ከጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤትም ሆነ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ የደረሰን ምንም ዓይነት ደብዳቤ የለም። እንደደረሰን የምናሳውቅ ይሆናል” ሲሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ምክትል ሳጅን ሳህለገብርዔል ይትባረክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፌዴራል አቃቤ ሕግም በተመሳሳይ ምንም ዓይነት ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እንዳልደረሰው አሳውቋል።

ቦንቱ በቀለ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከትናንት በስትያ ቂሊንጦ እስር ቤት አካባቢ በርካታ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸው በመግለጫው መሰረት ከእስር ይፈቱ እንደሆን በጉጉት ሲጠብቁ ነበር።

ሁኔታዎች መስመር ይዘው ማን ከእስር እንደሚፈታ ወይም ምህረት እንደሚደረግለት እስከሚታወቅ ድረስ ግን የታሳሪ ቤተሰብ እንዲሁም የወዳጅ ዘመድ ጉጉትና ጥበቃ ይቀጥላል።