ቀይ መስቀል ታግተው የነበሩ ቻይናውያንን ለኤምባሲያቸው መስጠቱን አረጋገጠ

ቀይ መስቀል ታግተው የነበሩ ቻይናውያንን ለኤምባሲያቸው መስጠቱን አረጋገጠ

ዓለም አቀፉ የቀይ መስል ማኅበር በምዕራን ኦሮሚያ ውስጥ ከሳምንታት በፊት ታግተው የነበሩ ቻይናውያንን መቀበሉን አረጋገጠ።

(bbc)—-የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አልዮና ሳይኔንኮ ለቢቢሲ እንደገለጹት ቀይ መስቀል ሦስቱን የቻይና ዜጎች ይዟቸው ከነበረው ታጣቂ ቡድን ተቀብለው ለአገራቸው ኤምባሲ አሳልፈው ሰጥተዋል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራውና መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለውና በቅርቡም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ቡድን ነው ብሎ የሰየመው ታጣቂ ቡድን፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቻይናውያኑን በቁጥጥሩ ስር እንዳስገባ አሳውቆ ነበር።

ቡድኑ በምዕራብ ኦሮሚያ መነ ሲቡ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ ውስጥ ያዝኳቸው ያላቸውን ሦስት የቻይና ዜግነት ያላቸውን ሰዎች መያዙን ከግለሰቦቹ ፎቶግራፍ ጋር አያይዞ ባወጣው መግለጫ አሳውቆ ነበር።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ አዲስ አበባ ያለው የቻይና ኤምባሲ ስለግለሰቦቹ በታጣቂው ቡድን እጅ መግባት በተመለከተ ያሉት ነገር አልነበረም።

ከሳምንታት በኋላ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ቡድኑ ቻይናውያኑን መልቀቁንና ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ማስረከቡን የሚገልጽ በሰነድና በፎቶግራፍ የተደገፈ መግለጫ አውጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ ቢቢሲ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ባደረገው ማጣራት በታጣቂው ቡድን ታግተው የነበሩት ሦስት ቻይናውያን ማዕድን አውጪ ሠራተኞች መቀበሉን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ አዲስ አበባ ለሚገኘው የአገራቸው ኤምባሲ ተላልፈው እንደተሰጡ የማኅበሩ ሕዝብ ግነኙነት ኦፊሰር አልዮና አስታውቀዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ታጣቂ ቡድኑ ቻይናውያኑን ስለማገቱ ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ አቅራቢያ “በመንግሥት እና በማዕድን አውጪዎቹ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ሕጋዊ አይደለም” በሚል ምክንያት ሠራተኞችን “አግቼ ይዣለሁ” ብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ የምዕራብ ወላጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በዞኑ ውስጥ ታግቶ የሚገኝ የውጭ ዜጋ የለም” በማለት ቡድኑ ያወጣው መግለጫ ሐሰት ነው ሲሉ ከሁለት ሳምንት በፊት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አቶ ኤሊያ ኡመታ በወቅቱ “በወረዳችን፣ በቀበሌያችን መሰል ነገር አለመከሰቱን አረጋግጠናል” ሲሉ ጨምረው ተናግረው ነበር። በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው ስለ ጉዳዩ የማውቀው የለም ብለዋል።

“ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች ታፍነዋል የሚል መረጃ የለኝም። ኦሮሚያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ መረጃው ይደርሰን ነበር” ብለዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ጥቃቶችን እንደሚፈጽም የሚነገረውና መንግሥት ‘ሸኔ’ እያለ የሚጠራው ቡድን በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ቡድን ተብሎ መፈረጁ ይታወሳል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር (አይሲአርሲ) ሕዝብ ግነኙነት ኦፊሰር አልዮና ሳይኔንኮ ማኅበሩ ሦስቱን ቻይናውያንን ተቀብሎ ለቻይና ኤምባሲ ማስረከቡን ጠቅሰው፤ “ማኅበሩ በኃላፊነቱ መሠረት ገለልተኛ ሆኖ ሦስቱ ቻይናውያን ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ለቻይና ኤምባሲ ተላልፈው እንዲሰጡ አስተባብሯል” ብለዋል።

የሕዝብ ግነኙነት ኦፊሰሯ አይሲአርሲ በጉዳዩ ላይ የነበረው ኃላፊነት ፍጹም ሰብዓዊነት ላይ የተመሠረት መሆኑን ገልጸው፤ ታግተው የነበሩት ቻይናውያን በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ በለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

ቢቢሲ በታጣቂዎች ተይዘው የነበሩትን ቻይናውያን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት ለማኅበሩ ያቀረበው ጥያቄ “ለግሰቦቹ ግላዊ መረጃ ጥበቃ” ሲባል የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪዋ ከመስጠት ተቆትበዋል።

በምዕራብ እና ደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል።

ለእነዚህ ጥቃቶችም ለረጅም ዓመታት በትጥቅ ትግል ላይ ከነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣውና እራሱን ‘የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት’ ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት ደግሞ ‘ሸኔ’ የተባለው ቡድን ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡድኑን የሽብር ቡድን አድርጎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መሰየሙ ይታወሳል።

በኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 18 የመንግሥት ባለስልጣናት፣ 112 የፖሊስ አባላት እና 42 የሚሊሻ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።