ስንብት ፣ ለመሰንበት ( ልደቱ አያሌው – የካቲት 29/2013 ዓ.ም.)

ስንብት ፣ ለመሰንበት
( ልደቱ አያሌው – የካቲት 29/2013 ዓ.ም.)
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሕልውና አደጋ ውስጥ ትገኛለች። ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የአቅምና የቅንነት ድክመት ያለበት በመሆኑ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ከማቃለልና ከመፍታት ይልቅ የበለጠ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። በዚህም ምክንያት ሀገራችን ሕልውናዋን የሚፈታተን አሳሳቢ የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባቷም በላይ ከኤርትራና ከሱዳን መንግሥታት ግልጽ ወረራ ተፈጽሞባታል። ከታሪኳና ከማንነቷ በተቃራኒም ይህንን ግልጽ ወረራ ለመቀልበስ የሚያስችል ዐቅምና ወኔ ያጣች ደካማ ሀገር ሆናለች። ይህ ክስተት ሀገሪቱ ምን ያህል በሒደት ውስጣዊ አንድነቷ እየተዳከመ እንደመጣና ወደ መበታተን አደጋ ውስጥ እየገባች ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።
 
ብልጽግና ፓርቲ እያራመደ በሚገኘው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ምክንያትም ሀገራችን ለከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ተጋላጭ በመሆን ብሔራዊ ጥቅሞቿንና ሉዓላዊነቷን በአግባቡ ማስከበር የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉም ሀገራዊ ሕልውናችንን በሚፈታተን መጠን ኢኮኖሚያችን ወደ ጥልቅ ቀውስና ኪሣራ ውስጥ እየገባ ይገኛል።
 
ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በብዙ የሕይወት መሥዋዕትነት የተገኘውና የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ተጀምሮ የነበረው የለውጥ ሒደት በአመራር ድክመትና በአምባገነናዊ ባሕርይ ምክንያት እንዲከሽፍ በመደረጉ ነው። በሥልጣን ላይ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ለለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ፖለቲካዊ ችግሮች ሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ከመፍታት ይልቅ አማራጭ ሐሳቦችን በማፈን፣ በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድና የፈጠራ ክስ በመመሥረት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ተቀናቃኞቹን በማሠርና ‘ለሕልውናዬ ሥጋት ናቸው’ ብሎ የሚፈራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ሕጋዊ ዕውቅና በመሠረዝ ጭምር ካለፈው የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ ሥርዓት የባሰ እንጂ የተሻለ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል። ባጭሩ፥ ሀገራችን ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ ወይም በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እየተመራች ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ የባሰ ቀውስ የመሸጋገር እንጂ ወደ በጎና የተሻለ ሥርዓታዊ ለውጥ የመሸጋገር ዕድል እንደሌላት በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ሆኗል።
 
እኔም ሆንኹ አባል የሆንኩበት ፓርቲ፣ በአንድ በኩል የተጀመረው የለውጥ ሒደት ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ምን ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦች በቅደም ተከተል መካኼድ እንዳለባቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት የተጀመረው የለውጥ ሒደት ከከሸፈ በሀገራችን አጠቃላይ ሕልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ምን ያህል ከባድና አደገኛ እንደሚሆን የሚያሳስብ የሐሳብ ትግል ላለፉት ሦስት ዓመታት ስናካሒድ ቆይተናል።
 
ነገር ግን የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ በዕውቀት፣ በምክንያታዊነትና በሐቀኝነት የሚካሄድ ሳይሆን ብሔርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ሤረኝነት፣ ጥላቻና ውሸት የነገሠበት በመሆኑ ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ሆኖም ቀደም ብለን ስናቀርበው የነበረው ስጋት ከተራ ሟርተኝነት ሳይሆን፥ ከተጨባጭ የፖለቲካ ግምገማ፣ ግንዛቤና ትንታኔ የመነጨ ስለነበር እንደፈራነው የለውጥ ሒደቱ ከሽፎ አሁን ሀገሪቱ ወደባሰና ውስብስብ የሕልውና አደጋ ውስጥ ገብታለች።
 
የለውጥ ሒደቱን መክሸፍ ተከትሎ ሀገራችን ወደ ከፍተኛ የርስ በርስ ጦርነት የገባችና በውጭ ኀይሎች ወረራ ሥር የወደቀች ቢሆንም ግብዞቹ የብልጽግና አመራሮችና የእነርሱ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆኑ ተከታዮቻቸው ግን ዛሬም ጭምር ሀገሪቱ ወደላቀ የብልጽግና ጎዳና እየገሰገሰች እንደሆነ ሊነግሩን ሲደፍሩ እያየን ነው። ብልጽግና ፓርቲ የከሸፈን የለውጥ ሒደት ተከትሎ የሚካሔድ ሀገራዊ ምርጫ፥ የተጨማሪ ቀውስ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግሮች የሚያስገኘው ምንም ዓይነት አዎንታዊ ፋይዳ የሌለ መሆኑን መገንዘብ ተስኖት የሥልጣን ቅቡልነት ልባስ ለመደረብ ሲል ብቻ ትርጉም የለሽ ምርጫ ለማካሔድ እየተጣደፈ ይገኛል። ይህም ሀገሪቱ ወደባሰና ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የፖለቲካ ቀውስ ልትገባ ትችላለች የሚል ተጨማሪና ምክንያታዊ ስጋት ፈጥሯል።
 
በእኛ በኩል ውጤታማ ሽግግር ባልተካሔደበትና አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በችኮላ ወደ ምርጫ ውስጥ መግባት አደገኛና ኀላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው የሚል የጠነከረ አቋም ያለን ቢሆንም ምርጫው መካሔዱ የማይቀር ከሆነ ግን ቢያንስ በምርጫው ሒደት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ ለመቀነስ በሚያስችል አግባብ በምርጫው ተሳታፊ ለመሆን በዝግጅት በማድረግ ላይ ነበርን።
ነገር ግን ከሁሉም ነገር በላይ ሐሳብን አብዝቶ የሚፈራውና ከሀገሪቱ ደኅንነት በላይ ለራሱ የሥልጣን የበላይነት ሰፍሳፋ የሆነው የወቅቱ መንግሥት በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሒደት ተሳትፎ እንዳይኖረን ስለፈለገና ስለወሰነ በሕገ ወጥ መንገድ ፓርቲያችን እንዲሰረዝና ከትግሉ ሜዳ እንዲወገድ አድርጓል።
 
በእኔ ላይም በባለቤትነት በሚቆጣጠራቸውና ለልዩ ተልዕኮ ባቋቋማቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ቅጥረኞቹን አሰማርቶ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሔድ፣ የዛቻና ማስፈራራት ድርጊት በመፈጸም፣ የፈጠራ ክስ በመመሥረትና በሕገ ወጥ መንገድ በማሠር የትግል ተሳትፎዬን ለመገደብ ሞክሯል። ይህም አልበቃ ብሎት በፖለቲካ መድረኩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም እንዳልኖር ስለፈለገ፥ ያለምንም ሕጋዊ ድጋፍ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ሕመም ወደውጭ ሀገር ሄጄ እንዳልታከም እገዳ ጥሎብኛል። ይህ ሕገ ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንና ባለሥልጣናትን ለማነጋገርና ለመማጸን ያደረግኩት ጥረትም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ የነበረኝ ቀጠሮ በመስተጓጎሉ በእያንዳንዱ ሰዓትና ዕለት ሕይወቴ ለዕልፈት ሊጋለጥ በሚችልበት አደጋ ውስጥ እገኛለሁ። በዚህ ድርጊቱም የወቅቱ መንግሥት አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ኢ ሰብአዊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በርግጥም ሥርዓቱ ከግለሰብ ግድያ ጀምሮ እስከ የሕዝብ ጅምላ ጭፍጨፋ ከሚደርስ ቀውስ የፖለቲካ ትርፍ ለመቃረም የሚጥር ኀይል በመሆኑ በእኔ ላይ ይህንን ማድረጉ እምብዛም አያስደንቅም።
 
ሰሞኑን የምገኝበትን አሳሳቢ የጤና ሁኔታ በተመለከተ ከሐኪም ጋር ባደረግሁት ምክክርም ለሕመሜ አስተማማኝ ሕክምና እስካገኝ ድረስ በአካሌም ሆነ በአዕምሮዬ ላይ ምንም ዓይነት ጫናና ውጥረት የሚፈጥር ሥራ እንዳልሠራና በቂ ረፍት እንዲኖረኝ ከባድ ማስጠንቀቂያና ምክር ተሰጥቶኛል። ጤናዬ ከሚገኝበት አሳሳቢ ደረጃ (Risk) አኳያ በሕይወት ለመሰንበት የምፈልግ ከሆነ፥ ለጊዜው ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ይህንን ማድረግ እንደሆነ ተነግሮኛል።
ሀገራችን የምትገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በእኔ በኩል አስቸኳይ የሕክምና ርዳታ አግኝቼና ጤናዬ ተስተካክሎ በትግሉ ሒደት የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረኝ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረኝና አሁንም ያለኝ ቢሆንም የሕክምና ዕርዳታ እንዳላገኝ ራሳቸውን በፈጣሪ ቦታ ሊተኩ በሚፈልጉ ገዥዎች በመከልከሌ ምክንያት ይህንን ምኞቴን ማሳካት የማልችልበት እንቅፋት ገጥሞኛል። ስለሆነም ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታ አግኝቼ ጤናዬ እስኪመለስ ድረስ በሕይወት የመሰንበት ዕድሌን ለመሞከር ስል ከማንኛውም ዓይነት የትግል እንቅስቃሴ (ገንዘብ ወይም ምክር ከማዋጣት ባለፈ) ራሴን ለጊዜው ለማቀብ የተገደድኩ ስለመሆኑ በከፍተኛ ቁጭትና ሐዘን እገልጻለሁ።
 
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰማኝ ቁጭትና ሐዘን ልብን የሚሰብር የሆነብኝ ያለምክንያት ሳይሆን፥ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕልውና አደጋ ውስጥ በገባችበትና ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ከአቅሜ በላይ በሆነ የጤና ችግር ምክንያት ራሴን ከትግሉ ሜዳ ለማግለል መገደዴ ያልጠበቅሁትና ከፍላጎቴ ውጭ የሆነ መጥፎ ገጠመኝ ስለሆነ ነው።
የሆነው ሆኖ ይህንን መጥፎ አጋጣሚ እንደ አንድ ጊዜያዊ ስንብት ልቁጠረውና ስለ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሕዝቡ ግንዛቤ ሊወስድ ይገባዋል ብዬ በማምንባቸው በሚከተሉት ስምንት ነጥቦች ዙሪያ የሚሰማኝን በመግለጽ ለመሰናበት ልሞክር።
 
1. ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለንም
 
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለገጠማት የሕልውና አደጋ በአስተሳሰብና በመዋቅር ደረጃ ዋናዎቹ ተጠያቂ ምክንያቶች የጽንፈኝነት ፖለቲካ፣ ብሔርተኝነትና የፖለቲካ አመራር ድክመቶች ናቸው። ስለሆነም ለወቅቱ የለውጥ ሒደት መክሸፍ ዋናው ተጠያቂ የእነዚህ መዋቅራዊ ድክመቶች ሰለባ የሆነው የቀድሞው ኢሕአዴግ፣ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ ነው። ብልጽግና ፓርቲ በእጁ የገባውን ወርቃማ የለውጥ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ተጨማሪ ምክንያትም ፓርቲው ከሀገሪቱ ጥቅምና ደኅንነት በላይ ለራሱ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ውስጣዊ አንድነቱን በማዳከሙና ወደ የርስ በርስ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ ነው። የፓርቲው ውስጣዊ ክፍፍል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ የርስ በርስ ግጭቶችና በትግራይ ክልል ለተከሰተው ጦርነት ዋናው ምክንያት ሲሆን ውስጣዊ ችግሩ አሁንም የተሻለ ትኩረት አግኝቶ ካልተፈታ በስተቀር ሀገሪቱን ለባሰ ቀውስና ጦርነት የሚዳርጋት ይሆናል። የራሱን ውስጣዊ ችግር መፍታት ያልቻለና ከራሱ የፖለቲካ ሥልጣን በላይ የሀገሪቱን ጥቅም ማስቀደም የተሳነው ደካማ ገዥ ፓርቲ የለውጥ ሒደቱን ስኬታማ ሊያደርግም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት አይችልም።
 
ቀደም ሲል ብልጽግና ፓርቲ ይህንን መሠረታዊ ድክመቱን አምኖ በመቀበልና በማረም ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት ይችላል የሚል ግምት (ምናልባትም የሞኝነት) የነበረን ቢሆንም ግምታችን ስህተት እንደነበር ያለፉት ሦስት ዓመታት ሒደት በተግባር አሳይቶናል። በዚህም ምክንያት ብልጽግና ፓርቲ እንደ ፈጣሪውና አሳዳጊው ህወሓት ሁሉ፥ ከመሞት መዳን ያለመቻል መዋቅራዊ ችግር ያለበት ግትርና ጀብደኛ ድርጅት እንደሆነ መገንዘብ ችለናል። ምክንያቱም ብልጽግና ፓርቲ አምባገነን የሆነው አምባገነን እንዲሆን ያስገደዱት ነባራዊ ሁኔታዎች ስላሉ ሳይሆን በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ አምባገነን መሆንን የመረጠ ድርጅት ስለሆነ ነው።
 
ከይቅርታ ጋር፥ እዚህ ላይ በከፍተኛ ድፍረትና ርግጠኛነት ልናገር የምችለው፥ የ21ኛዋን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን የማክያቬሊ የፖለቲካ ሤራ ስልት (Conspiracy Theory) እና የንግርት አምልኮት ለመግዛት እየሞከረ ያለው ብልጽግና ፓርቲ አሁን በያዘው አቅጣጫ መጓዝ ከቀጠለ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን የማፍረስ እንጂ ወደ ዘላቂ ለውጥ የማሸጋገር ሚና ከቶውንም ሊኖረው አይችልም። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ የገባንበትን ከባድ ጦርነት፣ በኤርትራናና በሱዳን መንግሥት የተፈጸመብንን ወረራ፣ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብጽና ከሱዳን ጋር የገባንበትን ፍጥጫ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየተፈጸመ የሚገኘውን የሕዝብ መፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በገዥው ፓርቲና በበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታየውን ፍጥጫ፣ ከዓለም ዐቀፉ ኅብረተሰብ እየደረሰብን ያለውን ከባድ ተጽዕኖ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለብን ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ፣ ከፊታችን እየመጣ ያለውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና ሌሎች ተመሳሳይ ፈተናዎቻችንን በጥቅሉ ደምረን ስናያቸው እንኳንስ ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ሆኖ ሁላችንም ተባብረን በአንድነት ብንቆም የወቅቱን የሀገሪቱን ፈተና በቀላሉ መወጣት አዳጋች ነው። ስለሆነም የውስጥ ችግራችንን ፈተን በአንድነት እስካልቆምን ድረስ በብልጽግና ፓርቲ የተናጠል ጥረት ችግራችን ፍጹም ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
 
2. ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰብና በሞራል ዝቅታ ላይ የምንገኝበት ነው
 
የምንገኝበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጭካኔን፣ ጅምላ ግድያን፣ የሤራ ፖለቲካን፣ የጥላቻ ንግግርን፣ ውሸትንና የግለሰብ አምልኮትን እየተለማመድን የምንገኝበት ነው። እነዚህን እኩይ ተግባራት በፊትአውራሪነት እያለማመደን የሚገኘው መንግሥት ሲሆን ጋሻጃግሬዎቹ ደግሞ ሃይማኖተኛ፣ ብሔርተኛና ምሁራን ነን ባይ “ልሂቃን” መሆናቸውን እያየን ነው።
በርግጥም ወቅቱ የ“ዝቅታችን” ወቅት ነው። ለአንድ “ሕወሓት” የተባለ አምባገነናዊ የሆነና በሕዝብ ትግል ከሥልጣን ለተወገደ ኀይል ባለን ገደብ የለሽ ጥላቻ ምክንያት ዐይነልቦናችን ታውሮ የዛሬ ገዥዎቻችን በሕዝብና በሀገር ላይ እየፈጸሙት ያለን የዛሬ ግፍና በደል ፈጽሞ ማየትና መረዳት ተስኖናል።
 
የወቅቱ ገዥዎቻችን ለራሳቸው የሥልጣን የበላይነት ሲሉ በሐሰትና በአስመሳይነት በጥብጠው የሚግቱንን ሥልታዊ ፕሮፓጋንዳ፣ በሀገር ጥቅምና በሕግ ማስከበር ሰበብ እየፈጸሙት ያለን በውጤቱ ሀገር በታኝ የሆነ የሤራና የበቀል ተግባር መገንዘብ ተስኖን እንደ ሕዝብ የአዲስ አምባገነናዊ ኀይል አዋላጅና ወላጅ ሆነናል። እወደድ ባይና ደካማ በሆነው የብልጽግና ፓርቲ አመራርና ተከታዮቹ በሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለው የጋራ አጀንዳ፥ በዋናነት ሕወሓትን በመጥላትና በመበቀል ዙሪያ የተቃኘ ቢሆንም ዋናውና የጋራ መገለጫቸው የሆነው ባሕርያቸውና ግብራቸው ግን የሕወሓት አውዳሚ አመለካከትና ውርስ (Legacy) አራማጅና አስቀጣይ መሆን ነው። እነዚህ ግብዝ ኀይሎች በሕወሓት መንገድ መጓዝ ሕውሓት በከፋፋይ አጀንዳው ያዳከማትን ሀገር ለይቶላት እንድትፈርስ ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ መገንዘብ ተስኗቸዋል። ይህም በራሱ ኢትዮጵያውያን ከሌሎችም ሆነ ከራሳችን ያለፈ ስህተትና ውድቀት የመማር አቅማችን እጅግ አናሳ መሆኑን ያሳያል።
 
በአጠቃላይም ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በራሳችን ታሪክ፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ሰላም፣ የወደፊት ዕድገትና ጥቅም ላይ ራሳችን ጦርነት ያወጅንበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል። በአጭሩ የራሱን ፍላጎትና ዘለቄታዊ ጥቅም የማያውቅ ግብዝ ሕዝብ ሆነናል። ከገባንበት ዝቅጠት ጥልቀትና ስፋት አኳያም አንዳንዶች “ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተጨራርሰን ከምንጠፋ በስምምነት ተለያይተን መኖር የምንችልበት ዕድል ይኖር ይሆን?” ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ የተገደዱበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያውያን እንደ “ሕዝብ” በዚህ ዓይነት የአስተሳሰብና የሞራል ዝቅታ ላይ እንደምንገኝ ተገንዝበን ስክነትና ብስለት ወደተላበሰ የፖለቲካ አቅጣጫ በፍጥነት ካልገባን በስተቀር ሀገራችንን ከገጠማት የመፈራረስ አደጋ ልንታደጋት አንችልም። እጅግ አማላይና መሠሪ በሆነው የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ስልት ሰለባ በመሆን፣ ወይም በአድር ባይነት፣ ወይም በጥቅመኝነትም ሆነ በማንኛውም ሌላ ምክንያት የወቅቱን ሥርዓት እየደገፍን የምንገኝ ዜጎች በታሪክና በትውልድ ፊት የየራሳችን የተጠያቂነት ድርሻ እንደሚኖርብን ተገንዝበን፥ ሥርዓቱን መቃወምና መታገል ቢያቅተን እንኳን ቢያንስ ዝም በማለት የሀገሪቱ ጥፋትና ውድቀት ቀጥተኛ ተጋሪ ከመሆን ልንቆጠብ ይገባል።
 
3. በይስሙላ ምርጫ የሚፈታ ችግር የለንም
 
ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል ውጤታማ የሽግግር ሒደት ባላካሔድንበት ሁኔታ የሚካሔደው የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ሒደትም ሆነ ውጤት የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ የማባባስ እንጂ የመፍታት አንደምታ አይኖረውም። ምርጫው ሳይጀመር ያለቀና ውጤቱም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ማስገባት ወይም አምባገነናዊነትን ማጽናት መሆኑ አስቀድሞ የታወቀ ነው። ይህ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም መንገድ አሸናፊ ሆኖ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል ወስኖና ተዘጋጅቶ የገባበት ምርጫ ስለሆነ፥ የዚችን ደሃ ሀገር በጀት ከማባከን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በአጭሩ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንደማይሆን ሳይሆን እንዳልሆነ የቅድመ ምርጫው ሒደት በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል። የወቅቱ የፖለቲካ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በአንጻራዊነት ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነትና በእኩልነት ምርጫ የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅን ለማስፈን፣ ብሎም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ በሚያስችል ሁሉን ዐቀፍ በሆነ የሽግግርና የሐሳብ ግብይት ሒደት (National Dialogue) ነው እንጂ በተለመደው ዓይነት የታይታ የምርጫ ግርግር አይደለም።
ወደ መዋቅራዊና ዘላቂ ለውጥ ለመግባት ከተፈለገ መፍትሔው የችኮላ ምርጫ ማካሔድ ሳይሆን በቅድሚያ ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በመላው ሀገሪቱ የታሠሩ የፖለቲከኛ እስረኞችን መፍታት፣ ዜጎች ላይ የሚደረግ አፈናና ግድያን ማስቆም፣ የሀገሪቱ ሕግጋትና ተቋማት ሀገር ጠቀም በሆነ አግባብ እንዲሻሻሉ ማድረግና ቢያንስ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት የታየው ዓይነት የዕርቅና የመቻቻል መንፈስ በሀገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል።
 
4. ልዩ ትኩረት አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ
 
በተግባር እየተፈጸመ ከሚገኘው ግልጽ ድርጊት እንደምንረዳው ብልጽግና ፓርቲ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ ሳይሆን በአፈናና በኀይል በሥልጣን ላይ ለመቀጠል የወሰነ አምባገነን ኀይል ነው። ገዥው ፓርቲ የሚጠላቸውንና የሚፈራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ መድረኩ በማስወገድና የፓርቲ አመራሮችን በማሠር በወሰደው ርምጃ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንዳልሆነ ከወዲሁ በተግባር አረጋግጧል። ሆኖም ምርጫው በታሰበበት ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሒደቱ ከማግለል ይልቅ አቅማቸውና ሁኔታው በፈቀደላቸው መጠን በምርጫው ተሳታፊ ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል እላለሁ።
 
ነገር ግን በቂ ዝግጅት አድርገውና የገዥውን ፓርቲ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በብቃት ተቋቁመው በሀገር ደረጃ መንግሥት ለመሆን በሚያስችል መጠን ምርጫውን ለማሸነፍ የሚኖራቸው ዕድል እጅግ ጠባብ መሆኑን በመገንዘብ ሙሉ ትኩረታቸውን አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አዲስ አበባ ከተማን አሸንፎ ለመረከብም አንድነት ተኮር የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመተባበር ጉዳይ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይገባና ምትክ የለሽ ርምጃ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ግለሰብን በመጥላት የሀገርን ጥቅም ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከማንኛውም ኀላፊነት ከሚሰማው ፓርቲ የማይጠበቅ ተግባር ቢሆንም ምናልባት የእኔ ለጊዜውም ቢሆን ከምርጫውና ከትግሉ ሒደት ገለል ማለት ለተቃዋሚው ጎራ መተባበር አንድ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።
 
የአንድነት ኀይሉ ምንም ዓይነት ድምጽ ሊባክን በማይችልበት ሁኔታ እርስ በርስ ላለመፎካከር አስቀድሞ ካልተስማማ በስተቀር፥ ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ (በፓርቲም ሆነ በግል የሚወዳደሩ) አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል እንደሚኖራቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል ካገኙም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ሕልውና አደጋ ውስጥ እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በምርጫ 97 ሲሆን እንደታየው “ምርጫው ስለተጭበረበረ ያሸነፍነውን ወንበር ወይም ምክር ቤት አንረከብም” በሚል የተሠራው ታሪካዊ ስህተት በዘንድሮውም ምርጫ እንዳይደገም ፓርቲዎች ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ መተማመንና መወሰን ይኖርባቸዋል።
 
5. መፍትሔው ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሽግግር ሒደት መፍጠር ነው
 
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በሁለት የጎረቤት ሀገራት (በኤርትራና ሱዳን) ሉዐላዊነቷ ተደፍሮ የግዛት ወረራ ተፈጽሞባታል። ይህ ወረራ ከማንኛውም ውስጣዊ ችግሮቻችን በላይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠውና በአስቸኳይ ሊቀለበስ የሚገባው ነው። ይህንን ማድረግ ሳንችል ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገርና ሕዝብ የነጻነት ታሪክም ሆነ ሉዐላዊ ሕልውና አለን ብለን መናገር አስቸጋሪ ይሆናል። የወቅቱ መንግሥት በሀገር ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ማስቆምም ሆነ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር ስላለመቻሉ የሚያቀርበው ማንኛውም ምክንያትም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የወቅቱ መንግሥትም ሆነ መንግሥትን በዋናነት የሚመሩት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እነዚህን ሁለት ቁልፍና መሠረታዊ የአንድ መንግሥት ኀላፊነቶች በአግባቡ መወጣት ስላልቻሉ ከእንግዲህ የሚኖራቸው ብቸኛ አማራጭ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሀገራዊ የሐሳብ ግብይት ሒደት (National Dialogue) መጀመርና ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሽግግር ሒደት ማካሔድ ነው።
 
የወቅቱ መንግሥት ቀደም ሲል በኢሕአዴግ ስም፣ አሁን ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ስም ሕዝባዊ ይሁንታ ሳይኖረው ለ30 ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለ ኅይል ነው። ይህ መንግሥት የሀገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ካለመቻሉም በላይ ይበልጥ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። ስለሆነም የወቅቱ ብልጽግና ፓርቲ በአንድ በኩል የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር ባልቻለበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አካሒዶ የሕዝብ እውነተኛ ውክልና ለማግኘት በሐቅ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን በቋሚ ርስትነት ይዞ ሊቀጥል አይገባውም።
ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ከግለሰብ በላይ የሆነ ሚና አለኝ ብሎ የሚያምንና ድክመቱ የኔ ሳይሆን የመሪዎቼ ወይም የመሪዬ ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነም ሀገሪቱ ለይቶላት ከመፍረሷ በፊት መሪዎቹን ወይም መሪውን የመቀየር ርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን ለሀገሪቱ ውድቀት ፓርቲውም እንደ ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል።
 
ከዚህ ውጭ በአንድ ሀገር የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና የውጭ ወረራን መከላከል ያልቻለ ማንኛውም መንግሥት በሥልጣን ላይ መቀጠል የሚችልበት ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት የለም። ከዚህ በተጻራሪ የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ መከላከል ያልቻለ መንግሥት፥ “ሌላ አማራጭ የለንም” በሚል ሰበብ በሥልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችለው ኢትዮጵያ ሕልውናዋን ከጥፋት አድኖ የሚያስቀጥላት ትውልድና ዜጋ ያልፈጠረች መካን ሀገር መሆኗን አምነን ከተቀበልን ብቻ ይሆናል።
 
በተጨማሪም በቅርቡ ትግራይ ክልል ውስጥ የገባንበት ጦርነት የሀገሪቱን አንድነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ የሚጥልና ከኛ ዘመንም አልፎ ምናልባትም ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ጣጣ የሚያስከትል አሳሳቢ ክስተት ነው። ስለሆነም ይህ ችግር በዘላቂነት በጦርነት ሊፈታ እንደማይችል በመገንዘብ ከሥልጣን ጥያቄ፣ ከበቀል፣ ከስሜትና ከጀብደኝነት በራቀ አተያይ ለችግሩ አስቸኳይ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል።
 
6. ሀገሪቱን ከሕልውና አደጋ መታደግ የሚችል ጠንካራ ፓርቲ መፈጠር አለበት
 
ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም በሀገሪቱ በጎ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የምንመኝና የምንፈልግ ቢሆንም ይህንን የሁልጊዜ ምኞታችንን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራና ለመርሕ ታማኝ የሆነ ፓርቲ መፍጠር እስካሁን አልቻልንም። ዛሬም እንደ ትናንቱ የሥርዓቱን ድክመቶችና ጥፋቶች ስንቆጥር የምንውል የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ብንኖርም ያለጠንካራ ፓርቲ መኖር ሀገሪቱን ከጥፋት መታደግም ሆነ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መገንዘብ የቻልን አይመስልም። በምሬት፣ በጩኸትና በውግዘት ብቻ ሊመጣ የሚችል ዘላቂ ለውጥ እንደማይኖር ተገንዝበን ለመጭው ትርጉም የለሽ ምርጫ ከምንሰጠው ትኩረት በላይ ለሀገሪቱ ችግሮች የሚመጥን ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ በመፍጠር ሥራ ላይ ማተኮር አለብን። በተለይም አንድነት ተኮር የሆነው የፖለቲካ ኀይል ከመቼውም ጊዜ በላይ በተዳከመበትና በተበታተነበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል አስተማማኝ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል በመገንዘብ አዲሱ ትውልድ ዋና ተዋናይ የሚሆንበት ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ መፍጠር ቀዳሚና ለነገ የማይባል አጀንዳችን መሆን ይገባዋል እላለሁ። ይህንን ማድረግ ካልቻልን “አማራጭ የለም” በሚል ሰበብ አምባገነኖችና የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ፓርቲዎች ወይም መሪዎች ሁልጊዜም በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉበትን ዕድል እንፈጥራለን።
 
7. የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ለሰላም
 
የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ በብዙ ውጥረቶች የተሞላና በቀላሉ ተሰባሪ ነው። በዚህ ምክንያት ውጤታማ በሆነ የሽግግር ሒደት ሳይታለፍ የሚካሔደው መጪው ምርጫ ሀገራችንን ወደ ባሰ ግጭትና ትርምስ ሊያስገባ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ። ይህ ስጋት በቂ መነሻ ምክንያት ያለው መሆኑን በመረዳት ሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች የምርጫ ሒደቱ ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዳያመራ የማድረግ የጋራ ኀላፊነት አለባቸው። ይህንን በመገንዘብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበትና የሰከነ ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ሊያካሒዱ ይገባል። አሁን ከምንገኝበት እጅግ ከባድና ውስብስ የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር የሰላም እጦት የሀገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን አደጋ ይዞብን ሊመጣ ስለሚችል፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫውን አሸናፊ ለመሆን ከመሥራት በላይ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።
 
በአግባቡ ካልተጠቀምንበትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ማኅበራዊ ሚዲያ የብሔራዊ ደኅንነታችን ዋና የአደጋ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ይህንን እውነታ በመገንዘብ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎቻችን በምርጫው ወቅት የሚኖራቸው ሚና ለሰላም ቅድሚያ በሚሰጥ የኀላፊነት ስሜት ሊካሔድ ይገባዋል። በአጠቃላይ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በውስጥም በውጭም ከፍተኛና አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል።
 
8. ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል የፖለቲካ ችግራችን አይፈታም
 
የወቅቱ የሀገራችን የፖለቲካ ችግር የሀገራዊ ብሔርተኞችንና የንኡስ ብሔር ብሔርተኞችን የተካረረ የፖለቲካ ቅራኔ በአንጻራዊነት በሚያቻችል አግባብ የወቅቱን ሕገ መንግሥት ከማሻሻል ባነሰ ሌላ የመፍትሔ ርምጃ ሊፈታ አይችልም። ሕገ መንግሥቱ እስካልተሻሻለ ድረስ ከማንነት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የተነሱትም ሆነ ወደ ፊት ባልተቋረጠ ሁኔታ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች የሀገሪቱን ሰላምና ሕልውና እያወኩ መቀጠላቸው አይቀርም። ይህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስም የሀገሪቱ ሰላም፣ አንድነት፣ ሕልውናና የኢኮኖሚ እጥረት በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም።
ከዚህ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ በኔ በኩል ለውይይት መነሻ የሚሆን የሕገ መንግሥት አማራጭ ረቂቅ ሰነድ በመጽሐፍ መልክ በማሣተም ላይ እገኛለሁ። የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፈታት የሚኖረውን ምትክ የለሽ አዎንታዊ አስተዋዕፆ የምትገነዘቡ መገናኛ ብዙሃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ዜጎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት በማድረግ ትችት እንድታቀርቡበትና እንድታዳብሩት፣ ከተቻለም ሰነዱን በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሒደት የጋራ የትግል አጀንዳ አድርጋችሁ እንድትጠቀሙበት በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
 
በመጨረሻም ከአቅም በላይ በሆነ የጤና ምክንያት ቢሆንም ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ለጊዜውም ቢሆን ከትግል ተሳትፎዬ ለመታቀብ በመገደዴ፥ የትግል አጋሮቼንና የዐላማ ደጋፊዎቼን ሁሉ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህንን የምለው ከእኔ ብዙ እንደምትጠብቁና ለእኔ ለራሴ እንደሆነብኝ ሁሉ ለእናንተም ይህ ክስተት ድንገተኛ መርዶ እንደሚሆንባችሁ ስለምገነዘብ ነው። ወደፊት የጤና ሁኔታዬ ተሻሽሎ እስከመጨረሻው በፖለቲካ ሒደቱ ለመቀጠል ለራሴ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም ፈጣሪ ዕድል እንደሚሰጠኝ ተስፋ እያደረግኹ ሀገራችን ኢትዮጵያ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማት ያለኝን ልባዊ ምኞት በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ።