ሰብዓዊነት ሲጠፋ የዜጎች መከራ “ቁጥር” ይሆናል!

ካምፓስ ውስጥ ለጥቂት ቀናት አርፈው ነበር። ያፈሩትን ሃብትና ንብረት ተዘርፈው፣ ነፍሳቸውን ለማዳን ሸሽተው የመጡ ናቸው። የደረሰባቸውን በደል፣ የተመለከቱትን ግፍና አሰቃቂ ድርጊት ለመናገር እንኳን ይሰቀጥጣቸዋል።

(ethiothinkthank) -አብዛኞቹ ደጋግመው የሚያነሱት “ISIS” የተባለው አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት በሀገር ልጅ፣ ያውም በወዳጅ ዘመድ ላይ በተግባር ሲፈፀም ማየታቸውን ለመናገር ከብዷቸው በሰቆቃ ይንገፈገፋሉ። በሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት መላ የሀገሪቱን ሕዝብ አስቆጥቷል፥ እጅግም አሳዝኗል። ነገር ግን፣ እዚሁ በሀገራችን ለዘመናት አብረው በኖሩ ህዝቦች መካከል ሲፈፀም ግን ነገሩ ሁሉ ቁጥር ይሆናል። ለምን?

አሰቃቂ ግፍና መከራ በአካል የደረሰበት ወይም በእውን የተመለከተን አንድ ሰው ብቻ ማናገር፥ ሰቆቃውን “እህ…” ብሎ ማዳመጥ በቂ ነው። በግፍ የሚፈፀም መከራና ስቃይን ለማውገዝና ለማስቆም የአንድ ሰው ቃል በቂ ነው። የደረሰበትን ችግር ከሰማነው፣ የአካሉን ጠባሳ ከተመለከትን፣ የስነ-ልቦና ጭንቀቱን ከተረዳን፣… እንደ ሰው ስለሚሰማን፥ እንደ ሰው ሰለሚያመን፥ እንደ ሰው ስለሚጨንቀን፣ … አዎ… የአንድ ሰው ቃል በቂ ነው!

ሰው በቋንቋ፥ ብሔር፥ ባህል፥ ልማድ፥…ወዘተ ይለያያል። ነገር ግን፣ እነዚህ ነገሮች የሰው ልጅን ተፈጥሯዊ ባህሪ አይቀይሩትም። የሰው ልጅ ሰብዓዊ ፍጡር ነው። እንደ ሰው በሰብዓዊነታችን ስናስብ በሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰውን መከራና ስቃይ “በእኔ ላይ ቢደርስ ኖሮ?” ብለን እናስባለን። የደረሰባቸውን መከራና ግፍ በራሳችን ላይ እናስበዋለን። ጭንቀትና ስቃያቸውን እንጋራቸዋለን። ይህ ሲሆን ግፍና በደልን አጥብቀን እናወግዛለን፣ ለማስቆም የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን።

በሰብዓዊነት ስናስብ ልክ በሊቢያ የተፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት በጋራ እንዳወገዝነው ሁሉ፣ በሶማሊና ኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢዎች የሚፈፀመውን ግፍና በደል በአንድ ድምፅ እናወግዛለን። ይህ ግን እየሆነ አይደለም። በሶማሊና ኦሮሚያ ህዝቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የሞቱት ሰዎች በሊቢያ ከተገደሉት ኢትዮጲያዊያን አስር እጥፍ ይበልጣል። በዚህ ምክንያት የተፈናቀሉት ሰዎች ከ60 ሺህ በላይ ሆኗል።

በሶሚሊና ኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢዎች በተነሳው ግጭት ምክንያት በመፈናቀል ላይ ያሉ ሰዎችን የሚያሳይ ፎቶ (ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ)

ለአንድ እናት ልጇ የተገደለው ሊቢያ ሆነ ጅግጅጋ ልዩነት የለውም። ቀሪ ዘመኗን በሃዘን ተቆራምዳ ትኖራለች። እስኪ እናታችሁ የእናንተን ሞት ብትሰማ እንዴት እንደምትሆን አስቡት? በዚህ ግጭት ምክንያት ልጇ የተገደለባት እናት እኮ ልክ እንደዛ እየሆነች ነው። ብዙዎቻችን ይህን መከራና ስቃይ በራሳችን አናስበውም። ከዚያ ይልቅ፣ የሞቱት፥ የተፈናቀሉት፥ የተጎዱት፥… በሙሉ ቁጥር ናቸው። ሚዲያው የሚዘግበው ቁጥር ነው! የመንግስት አካል የሚያጣራው ቁጥር ነው። ዜጎች የሚያሰሉት ቁጥር ነው። ምክንያቱም የገደለው ሆነ የሞተው ብሔር ነው። ይህን ያህል “ኦሮሞ፥ ሶማሊ፥ ሲዳማ፥… ሞተ፥ ተጎዳ፥ ተፈናቀለ” ሲባል በእኔነት ከማሰብ ይልቅ የተጎጂ ቁጥር መቁጠር ጀምረናል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በጉዳዩ ዙሪያ ለVOA የሰጡት አስተያየት

በአጠቃላይ ሰብዓዊነት ከውስጣችን ተንጠፍጥፎ አልቋል። በሰዎች ላይ የደረሰን መከራና ስቃይ ለማውገዝ በብሔር ማስላት ልማድ ሆኗል። ሰብዓዊነታችንን አውልቀን የብሔር ጭብል አጥልቀናል። እውነት በብሔር፣ መከራና ስቃይን በቁጥር ማስላትና መገንዘብ ከጀመርን ቆይተናል። ፍፁም ስሜት አልባ ፍጡሮች ሆነናል። እንደ ሰው ማሰብ ተስኖናል።