ሰበር ዘና ከኤጄቶ አጠቃላይ ስብሰባ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ሰበር ዘና ከኤጄቶ አጠቃላይ ስብሰባ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ከመላው የሲዳማ አከባቢዎች የተወጣጡ የኤጄቶ ተወካዮች እና የሀዋሳ ከተማ እና አከባቢዋ ኤጄቶች በአንድነት ዛሬ ሰኔ 27 በሀዋሳ ሚልንየም አዳራሽ ባደረጉት አጠቃላይ ስብሰባ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። እኛ የሲዳማ ኤጄቶች የሲዳማ ጥያቄና ጥያቄው የሚፈታበት ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገራዊ ለውጡን በማይናድ መሰረት ላይ የሚገነባና ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝሙን የሚያጠናክር ኩነት መሆኑን እናምናለን። ይህን ጥያቄ ላለመለስ የሚደረጉ ማቅማማቶች የለውጥ እሳቤውንና ህገ መንግስቱን በገሀድ እንደመጻረር ይቆጠራል።

ይህ ጥያቄ በአግባቡ ተመልሶ ከውጥረት ማእከልነት ወደ ሰከነ ፖለቲካዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚወስድ ለውጥ እንዲሆን ለማድረግ የሲዳማ ህዝብ አለምን ያስደመመ ሰላማዊ ትግል ሲያደርግ ከርሟል። ይህ ግዜ ትግላችን ፍሬ አፍርቶ ሊያጎመራ የተቃረበበትና ነጻነታችን እውን ሊሆን ቀናቶች የቀሩበት ግዜ ነው። ከዚህ ግዜ መቃረብ ጋር ተያይዞ ያሉትን ብዥታዎች
ለማጥራት በሚከተሉት ጉዳዮች የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎችን እናሰማለን።

1, 11/11/11 የሲዳማ ህዝብ ደቡብ ከሚባል ድሪቶ ውስጥ ለማደር የማይገደድበትና በራሱ እጣ ፈንታ ላይ በራሱ ምክር ቤት ራሱ ብቻ የወሰነበትን ውሳኔ የሚያጸናበት ቀን ነው። ይህን የነጻነት ቀን ለማጨለምና በተንሸዋረረ መልኩ የተረዱ አካላት ይህን ቀን የአለም ፍጸሜ በማስመሰል የሚያሰሙትን ተራ ፕሮፓጋንዳ አምርረን እንቃወማለን። በዚህች ቀን ነውጥ እንደሚኖር ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚፈናቀሉና የመንግስት ተቋማት እንደሚወድሙ የሚዘክሩ አካላት መኖራቸውን እያስተዋልን ሲሆን እንዲህ ያለ እሳቤ 1 ህግን ለማስከበር በሚል ሰበብ ህዝብ እንዲጨፈጨፍና ጥያቄያችን እንዲቀለበስ የቋመጡ ሀይሎች
መሆናቸውን ደርሰንበታል። በመሆኑም ለጠላት ሴራና ወጥመድ የሚመች ምንም አይነት አውድ እንዳይኖር አምርረን የምንታገል መሆኑን አጥብቀን የምንታገል ይሆናል::

#2) የሲዳማ ክልል ጥያቄን አስመልክቶ ከየትኛውም አካል የሚሰጥ ኢ-ህገመንግስታዊ፡ምላሽ ምንም አይነት ተቀባይነት ይኖረውም። ይህ በንዲህ እንዳለ ጥያቄያችንንና ውሳኔያችን ለመቀልበስ የሚነዙ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች የሲዳማን ህዝብ ጥንታዊ የጀግንነት ስነልቦናን በጉልህ ካለመገንዘብ የሚመነጩ ተራ ፉከራዎች እንደሆኑ እንገነዘባለን። ከዚህ ጋር ተያያዞ
ከቅርብ ግዜ ወዲህ አንዳንድ ሀይሎች በግንባር ቀደምት ኤጄቶች ላይ ለማድረስ እየሞከሩ ያሉት ዛቻና የግድያ ሙከራ አጥብቀን የምንቃወም ከመሆኑ ባሻገር እንደዚህ አይነት ሙከራዎች ከተደገሙ መዘዛቸው ስለሚከፋ ለማናቸውም ሀይሎች ጠቃሚ ስላልሆኑ እንዳይሞከሩ አናስጠንቅቃለን።

3) ከቅርብ ግዜ ወዲህ በውስጣዊ እና ውጫዊ ሀይሎች ተዋናይነት እና ደኢህዴናውያን አቀናባሪነት በሲዳማ ህዝብ መካከል ልዩነት እንዳለ አስደርገው ለማስደለቅ የሞከሩት ውሃን የመውቀጥ ዘመቻ ከንቱ ህልም፡መሆኑን ኤጄቶ አበክሮ ያስገነዝባል። የሲዳማ ህዝብ ከአንድ ወንዝ የተቀዳ ከባህር የጠለቀና የሰፈረ አንድ ህዝብ ነው።የሲዳማ ህዝብ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ አንድነቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ አያውቅም። የሲዳማ ህዝብ አንድ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አንድ አይነት ህዝብ መሆኑን ዳግም ለአፓርታይድስቶች በሚገባቸው መልኩ ልንነግራቸው እንፈልጋለን። በመጨረሻም የሲዳማ ህዝብ ነጻነቱን እውን ለማድረግ ከርሞ ከከፈለው ዋጋ በላይ  አይከፍልም። በባርነትና በውርደት ግዞት ውስጥ ከመኖር የሚበልጥ ዋጋ የሚያስከፍል ነገርም
የለም። ህዝባችን ጥያቄውን ዳግም እንዳያነሳ ዛቻና ማስፈራሪያ ባለፈ ታንክና መድፍ የጄት ድብደባና ጂ 3ን ያላስተናገደበት ዘመን የለም። ያልተጋፈጥነው ያልቀመስነው ፈተና ባለመኖሩ  ለመጋፈጥ የምንፈራውም ምንም አይነት ምድራዊ መከራ እንደማይኖር ለሚመለከተው ሁሉ ማሳወቅ እንወዳለን።

Sidama page


የፊታችን ሀምሌ 11፤ 2011 ዓም የሲዳማ ህዝብ አሁን ባለዉ የደቡብ መስተዳደር ስር ለማደር የማይገደድበትና በራሱ ዕጣ ፈንታ ላይ በራሱ ምክር ቤት ራሱ ብቻ የወሰነበትን ውሳኔ የሚያጸናበት ቀን ነው ሲል ኤጄቶ የተባለው የሲዳማ የመብት አቀንቃኝ ቡደን አስታወቀ። ቡድኑ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ከአባላቱ እና ከደጋፊዎቹ ጋር መወያየቱን በመግለፅ የሲዳማ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ዙሪያ ያለውን አቋም በማኅበራዊ ድረ ገጹ ይፋ አድርጓል። በዚሁ መግለጫው አንዳመለከተው የሲዳማ ኤጄቶች የሲዳማ ጥያቄ እና ጥያቄው የሚፈታበት ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገራዊ ለውጡን በማይናድ መሠረት ላይ የሚገነባና ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን የሚያጠናክር ኩነት መሆኑን እናምናለን ብሏል። 

የሲዳማ ክልል ጥያቄን አስመልክቶ ከየትኛውም አካል የሚሰጥ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፡ ምላሽ ምንም አይነት ተቀባይነት አይኖረውም ያለው መግለጫው ጥያቄያችንን እና ውሳኔያችንን ለመቀልበስ የሚነዙ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች የሲዳማን ሕዝብ ጥንታዊ የጀግንነት ስነልቦና በጉልህ ካለመገንዘብ የሚመነጩ ተራ ፉከራዎች እንደሆኑ እንገነዘባለን ሲልም አትቷል።
የሲዳማን ሕዝብ የነጻነት ቀን ለማጨለም እና ሃሳቡንም በተንሸዋረረ መልኩ የተረዱ አካላት ይህን ቀን የዓለም ፍጸሜ በማስመሰል የሚያሰሙትን ተራ ፕሮፓጋንዳ አምርረን እንቃወማለን ሲል መግለፁን ከሐዋሳ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሰኞ ለአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት ዓመታዊ የሥራ ዘገባ ባቀረቡት ወቅት ሲዳማን ጨምሮ በክልል ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች ለጥያቄያቸው ምላሽ እስኪሰጥ በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቀዋል። ከዚህ ውጭ በኃይል እና በደቦ ለማስፈጸም የሚሞክሩ አከላት ካሉ መንግሥታቸው ሕግ ለማስከበር ወደኋላ እንደማይል ማስጠንቀቂያ አዘል የሚመስል ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሉ የሚታዩ ሽኩቻዎች የሀገሪቱን አለመረጋጋት እንዳያባብሱት ዓለም አቀፉ የቀውስ አጥኚ ቡድን አሳሰበ። ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ የሲዳማ ሕዝብ መሪዎች ለጥያቄያቸው የፌደራል መንግሥትን አዎንታዊ ምላሽ ካላገኙ ከፊል ራስገዝ አስተዳደርነትን በመጪው ሐምሌ አጋማሽ ለማወጅ መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል። ለተባለው ወሳኝ ቀን የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ቢቀርም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት ቀን እንዳልቆረጡ እና ዝግጅትም እንዳላደረጉ ቡድኑ ይፋ ባደረገው ዝርዝር ዘገባ ጠቅሷል። ጉዳዩ በአግባቡ ካልተያዘ በሲዳማ በኩል የሚታየው ፍላጎት አመፅን በማቀጣጠል የሀገሪቱ ጥምር መሪ ፓርቲ የገጠመውን ቀውስ ሊያባብስ እንደሚችል ክራይስስ ግሩፕ አመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢል አህመድ እና የግንባሩ መሪዎች ከሲዳማ ሕዝብ መሪዎች ጋር የሚግባቡበትን መንገድ እንዲፈልጉ እና ቆየት ብለውም ለሕዝበ ውሳኔው ቀን መቁረጥ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

DW Amharic