ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በኢዜማ መነጽር

ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በኢዜማ መነጽር

በአስረስ አያሌው

(ethiopianreporter)—አገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 1964 ድረስ ለትራፊክ እንቅስቃሴ የምትጠቀመው የመንገዱን ግራ (Left Hand Traffic) ነበር። በዚያ ዓመት የትራፊክ እንቅስቃሴውን ከግራ ወደ ቀኝ (Right Hand Traffic) አዙራለች። ከዚህ ጊዜ ብዙም ሳይቆይ ሌላ የመስመር ለውጥ በአገራችን ውስጥ ተከስቷል። ይህም የብሔር ብሔረሰቦች መብት ዋነኛው የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ወደ መድረክ ብቅ ባለ ጊዜ ነው። የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ የሚባል ነገር የለም፣ ያኔም ሆነ ዛሬ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ናቸው ያሉት በማለት ጥያቄውን ለማዳፈን መሞከር፣ በቀኝ በኩል በሚያስኬድ መንገድ ላይ በግራ በኩል ለማሽከርከር እንደ መሞከር ነው። ውጤቱ አስከፊ አደጋ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ወደድንም ጠላንም የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለቀጣይ በርካታ አሥርት ዓመታት የአገራችንን የፖለቲካ መልክዓ ምድር (Landscape) ተቆጣጥሮት ይዘልቃል።

ይህን ጽሑፍ ለማሰናዳት የገፋፋኝ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያወጣው መግለጫ ነው። ርዕሱ ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈውና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው!›› ይላል። በመግለጫው የተዳሰሱት ሁለት አንኳር ነጥቦች፣ ገዥው ፓርቲ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የወሰደው ዕርምጃና የደቡብ ክልልን በክላስተር አወቃቀር በአዲስ ሁኔታ ለማደራጀት ያቀረበው ሐሳብ ናቸው። በእውነቱ ኢዜማ እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ መንግሥትን መተቸቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። የንጉሥ አጫዋችነት ለመኢሶንም አልበጀ።

ኢዜማ ገዥው ፓርቲ ሥልጣኑን ለማራዘም የሄደበትን መንገድ አስመልክቶ የሰነዘረውን ትችት እኔም እጋራዋለሁ። ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባይጠፋም እንኳ በተጨማሪ ጥንቃቄ፣ ጊዜና በጀት ምርጫውን ማድረግ የሚቻልበት አማራጭ እንዳለ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለጸ ማግሥት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜም ሆነ የመንግሥትን ሥልጣን ያልገደበ ውሳኔ ማስተላለፉ በእርግጥም ኢዜማ እንዳለው ‹‹ግልጽ ያልሆነ ዓላማ እንዳነገበ›› የሚያስጠረጥር ነው።

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ወቀሳ ከኢዜማ ሲደመጥ ያስተዛዝባል። ምክንያቱም ኢዜማ፣ ‹‹ሥልጣን ላይ የወጣው ኃይል ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዙ ሥራዎች ለመሥራት ቃል እስከ ገባና ይህንን ቃል የሚጠብቅ እስከሆነ ድረስ፣ በረጅም ጊዜ ቀስ በቀስ የሚገነባ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከፉክክር ውጪ በሆነ መንገድ ማገዝ እንደሚያስፈልግ›› የሚያምን ፓርቲ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዚህ የተለየ አቋም ሲያንፀባርቅ አጋጥሞኝ አያውቅም። ከዚህ አንፃር አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ‘ረጅም ጊዜ’ የሚወስድ እንደ መሆኑ መጠን፣ አሁን ያለው መንግሥት በውል ላልታወቀ ጊዜ በሥልጣን ላይ ቢቆይ ኢዜማ አይቃወምም ብል ስህተት አይሆንብኝም። ታዲያ የአሁኑ ተቃውሞ ከየት የመጣ ነው?

መግለጫው ኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑን ከናካቴው ረስቶት እንደ ከረመ ያሳብቃል። ዕገዛ ማድረግ የሚመሠገን ተግባር ነው፡፡ ሆኖም የኢዜማ ዓይነት መርህ አልባ ዕገዛ ቢቀር ይሻላል። ለመሆኑ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚፈጀው ‘ረጅም ጊዜ’ በትክክል ርዝመቱ ምን ያህል ነው? ‹‹ከፉክክር ውጪ በሆነ መንገድ›› ሲባልስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ምርጫ መካሄድ የለበትም ማለት ነው? ተቋማት በዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ በማለፍ ስህተታቸውን እያረሙ ካልሄዱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በምን መሠረት ላይ ነው የሚገነባው? ይህን ሁሉ ኃላፊነትስ ለአንድ ፓርቲና ግለሰብ መተው ትክክል ነው? ደግሞም ይህ ፓርቲና ግለሰብ ኢዜማ አጥብቆ የሚያወግዘውን የዘውግ ፖለቲካ እንደሚያራምዱ መረሳት የለበትም። የኢዜማ ዕገዛ መርህ አልባ ነው የምለው ለዚህ ነው።

የኢዜማ መግለጫ መንግሥት ሥልጣኑን ያራዘመበትን መንገድ በጥቂቱ ተችቶ፣ በስፋት የዳሰሰው የደቡብ ክልል በክላስተር አወቃቀር እንደገና ሊደራጅ የመሆኑን ጉዳይ ነው። መግለጫው ከርዕሱ ጀምሮ ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ዕውቅና የሚሰጥ ይመስላል። ይሁንና ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ኢዜማ ለዚህ መሠረታዊ መብት ፈጽሞ ደንታ እንደሌለው እንገነዘባለን። በበኩሌ የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚለው ጎራ በአገሪቱ ካለው እውነታ ጋር ምን ያህል እንደተራራቀ የሚያሳይ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር ግልጽ ጥያቄዎች እንደቀረቡ ኢዜማ አመልክቷል። ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ጥያቄዎቹ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ የተመሠረቱትም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ በሰፈረው አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ነው። ይሁንና ኢዜማ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን እንደሚደግፍ የተናገረውን ቃል ወዲያው በማጠፍ፣ ‹‹ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በተግባር የተፈተሸው ሕገ መንግሥት›› ይህን ጥያቄ እንደማይመልስ ለማስገንዘብ ይሞክራል። ጥያቄው ክልል የመመሥረት ነውና ከዚህ ርዕስ ሳንወጣ፣ ለመሆኑ አንቀጽ 47 ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በተግባር ተፈትሾ ውድቅ የሆነው መቼ ነው? ክልል የመሆን ሕዝበ ውሳኔስ ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በቀር መቼ ተካሂዶ ያውቃል? በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ችግሩ ያለው ከአንቀጽ 47 ሳይሆን አንቀጹ ተፈጻሚ ሆኖ አለማወቁ ላይ ነው።

መግለጫው በመቀጠል፣ ‹‹በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት አሁን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ‘ክልል እንሁን’ የሚል ጥያቄ ያስገቡት ዞኖችን ክልል እንዳይሆኑ ለመከልከል ምንም ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት የለም፤›› ይላል። እንዲያማ ከሆነ ኢዜማ በክልል መደራጀትን ይደግፋል ማለት ነው ብለን ሳናበቃ መልሶ ሕጉ “ክፍተት አለበት” ይለናል። ክልል መሆንን የሚከለክል ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት እንደሌለ ከመሰከሩ በኋላ፣ ክፍተት አለበት ማለት በአንድ ራስ ሁለት ምላስ መሆን ነው። ዓይናችንን ካልጨፈንን በቀር አንቀጽ 47 ምንም ዓይነት የሕግ ክፍተት የለበትም። ‹‹መጨረሻ የሌለው የማንነት፣ የክልልነት፣ እንዲሁም የአገር እንሁንነት ጥያቄዎችን ያስከትላል›› የሚለው ሙግትም የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለመጨፍለቅ የሚቀርብ ማመካኛ ነው። ክልል ለመሆን የጠየቁት፣ መሥፈርቱንም የሚያሟሉት ሁሉም ብሔረሰቦች እንዳልሆኑ ኢዜማ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢዜማ አንቀጽ 47ን አያውቀውም፣ ወይም ለአንቀጹ ከፍተኛ ንቀት አለው። ይህን ለማለት ያበቃኝ፣ ‹‹በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በሕዝብ ቁጥር አነስተኛ የሆኑ አካባቢዎችን በክልልነት ሲያካልል፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን አካባቢዎች በመጨፍለቅ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን መሥርቷል፤›› የሚለው ክሱ ነው። በቅድሚያ ኢዜማ ያላስተዋለው ነገር ክልል የመሆን መብት የተሰጠው “ለአካባቢዎች” ማለትም ለአምባ፣ ለሸለቆ፣ ለሜዳ፣ ለወንዝ፣ ለተፋሰስ፣ ለተራራ፣ ለሸንተረር አልያም ለሌላ ዓይነት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳይሆን ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው። ኢዜማ ተደናግሮ ይሁን ሲያደናግር ባይታወቅም፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች በደቡብ ክልል ውስጥ እንደ ተጨፈለቁ መስክሯል። እና ታዲያ መፍትሔው የራሳቸውን ክልል መመሥረት ነዋ! አራት ነጥብ።

ይሁን እንጂ ኢዜማ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን እደግፋለሁ ያለው ለይምሰል መሆኑን ለመረዳት፣ ‹‹ዘውግን መሠረት አድርጎ የሚደረግ የአስተዳደር አከላለል ራስን በራስ ከማስተዳደር ይልቅ፣ አካባቢውን ለዘውግ ማንነት የባለቤትነት ካርታ መስጫ መንገድ ነው፤›› በማለት የተናገረውን ሐሳብ መመልከት በቂ ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሕዝቡ ክልል የመሆን መብቱን ለመጠየቅ ግልብጥ ብሎ አደባባይ የወጣው በየዘውጉ አልነበረም? ጥያቄ ያቀረቡት ዞኖችስ በዘውግ የተዋቀሩ አይደሉም? ዘውጌያዊ የክልል አደረጃጀት የሕዝቡ ፍላጎት ባይሆን ኖሮ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በ99.6 በመቶ ድምፅ ይፀድቅ ነበር? የባለቤትነት ካርታ መስጫ ነው የተባለውስ ማን ሰጪ? ማን ተቀባይ ሆኖ ነው? ብሔሩ ቀድሞውንስ ቢሆን የሠፈረበት መሬት ባለቤት አይደለም?

በሐሳቡ የማይረጋው ኢዜማ፣ ‹‹የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን የዜጎችን ደኅንነት፣ የአገር ሉዓላዊነትንና ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ከማድረግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብቻ›› እንዲገደብ የሰጠውን ማሳሰቢያ ዘንግቶ፣ መንግሥት ‹‹ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛና ዘላቂ መፍትሔ መስጠት›› ይገባዋል ይላል። ወዲያው ደግሞ እጥፍ ብሎ፣ ‹‹የዜጎች ሕጋዊ የሥልጣን ባለቤትነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት ዘላቂ ውጤት ያለው ውሳኔ የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄ›› አይመልስም ብሎ ያርፈዋል። ኢዜማ ሆይ፣ የትኛውን ሐሳብ እንቀበል? መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ውሳኔዎች ይስጥ? ወይስ አይስጥ?

ኢዜማ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የዜጎችን መብት ሊያስከብር እንደማይችል የማመን መብት ቢኖረውም፣ ትልቁ ስህተቱ ይህ ሕገ መንግሥት ጥያቄዎቼን ይመልስልኛል ብለው የሚያምኑ ሕዝቦች መኖራቸውን መካዱ ነው። በዚህ አቋሙ በደቡብ ክልል የሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።

ኢዜማ መግለጫውን ሲደመድም፣ ‹‹ደቡብ ክልል የሕዝቡን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንደገና እንዲዋቀር እንደሚፈልግ›› ገልጿል። ይህ የመፍትሔ ሐሳብ ከመንግሥት የክላስተር ምክረ ሐሳብ ፈጽሞ ያልተለየ፣ ይልቁንም የመግለጫውን ባዶነት ያጋለጠ ነው። ‹‹በጥያቄያችሁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጋችሁ በሕዝበ ውሳኔ መወሰን የምትችሉበት ሁኔታ እስኪመቻች በትዕግሥት ጠብቁ›› የሚለው ማባበያም ከንቀት ያለፈ ሌላ ሊሆን አይችልም። የሕዝቡ ፍላጎት ክልል መሆን እንደሆነ ከተረጋገጠ ቆይቷል። ሕዝበ ውሳኔ እንጂ ውይይት ይካሄድልኝ አላለም። ኢዜማ ሕዝቡን አይወክሉም ያላቸው የዞን አመራሮች እንዳሁኑ ጊዜ የሕዝብን ጥያቄ አንግበው በቆራጥነት የታገሉበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም። ከሰሞኑ እንኳ የወላይታ ዞን 38ቱም ተወካዮች የሕዝባቸው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሊደመጥ ስላልቻለ፣ ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ራሳቸውን ማግለላቸውን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

ለማጠቃለል ክልል የመሆን መብት ሕገ መንግሥታዊ እንደ መሆኑ መጠን፣ ሕገ መንግሥታዊ መልስ ያሻዋል። የአንድ ብሔር ጥያቄ ብቻ ተመልሶ የሌላው በጥናት ይመለሳል ማለት ዓይን ያወጣ መድልኦ ከመሆኑም በላይ፣ ሕዝባዊ ተቃውሞ ቀስቅሶ የአገርን ሰላም ከማደፍረስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ስለዚህ መንግሥት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ክልል ለመሆን ጥያቄ ላነሱ ዞኖች በሙሉ፣ ጥያቄ እንዳቀረቡበት ቅድም ተከተል ሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት የዘመናት ጥያቄያቸውን ሊመልስላቸው ይገባል። በዚህ መንገድ ጥያቄው የፖለቲከኞች ይሁን ወይም የሕዝብ በማያጠራጥር ሁኔታ ግልጽ ይሆናል። ደግሜ እላለሁ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዓ ምድር ወደነበረበት ላይመለስ ተቀይሯል። በቀኝ በኩል በሚያስኬድ መንገድ ላይ በግራ በኩል ማሽከርከር ለግጭት እንደሚዳርገው ሁሉ፣ ይህን ሀቅ መካድም ትርፉ አላስፈላጊ ግጭትና ብጥብጥ ነው።


 

የራስን ዕድል በራስ መወሰን በኢትዮጵያ: ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ መመለስ ባሻገር #BBS