ረጋቱ ሮባ- ሞገደኛዋ ኮማንደር:-ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

ረጋቱ ሮባ- ሞገደኛዋ ኮማንደር

ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

ለኢህአፓ ሰዎች “የድርጅታችሁ ትልቋ የሴት ሰማዕት ማን ናት?” የሚል ጥያቄ ብታቀርቡላቸው “ዳሮ ነጋሽ” የሚል መልስ እንደሚሰጧችሁ ይታወቀኛል፡፡ በርግጥም ወ/ሮ ዳሮ ነጋሽ ገድሏ ሊደነቅ የሚገባው ታላቅ ሴት ነበረች፡፡ የሕወሐት ሰዎች ደግሞ “Martha” ለተሰኘችው ሴት ታጋይ ልዩ ክብር አላቸው፡፡

የኦነግ ሰዎች በበኩላቸው ትልቋ የሴት ሰማዕታቸው “ጁኪ በሬንቶ” መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ “ጁኪ” እላይ ከተገለጹት ሰማዕታት የምትለየው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል ሆና ራሷን ለአደጋ በማጋለጧ ነው፡፡ በወቅቱ የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረችው ጁኪ የደርግ ልዩ የኮማንዶ ብርጌድ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ገላሳ ዲልቦን ጨምሮ በርካታ የኦነግ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተቃረበበት ሁኔታ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እልህ አስጨራሽ ውጊያ አድርጋ አደጋውን ለመቀልበስ ችላለች (ጁኪ መሪዎቹን ከሀረርጌ ወደ ባሌ ካሻገረች በኋላ ራሷን ገድላለች፤ ደርጎች ግን “ጁኪን እኛ ነን የገደልናት” በማለት በሀረርጌ ክፍለ ሀገር ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ አካሄደዋል)፡፡

በመግቢያዬ ስለጁኪ በሬንቶ የጠቀስኩት “ረጋቱ” የምትባለው ሞገደኛ ሴት በርሷ ገድል ተነሳስታ ወደ ትግል ሜዳ የወጣች በመሆኗ ነው፡፡ በርግጥም ጁኪ በሬንቶ ስትሞት በርካታ የኦሮሞ ሴቶች የኦነግን ጦር ተቀላቅለዋል፡፡ ደርግ የጁኪን መስዋዕትነት እንደ አልባሌ ነገር በመቁጠር በርሷ ዝና ላይ አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ቢሞክርም ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው የሆነበት፡፡ በአንዷ ጁኪ እግር በርካታ አስገራሚ የሴት ታጋዮች ናቸው የተተኩት፡፡ አስሊ፣ ጫልቱ፣ ዋሪቱ፣ ኢብሲቱ፣ ኩለኒ፣ ዱርሲቱ፣ ኦብሲቱ፣ ወዘተ… ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከነርሱ መካከል ሀገርን ጉድ ያሰኘችው ግን “ረጋቱ” ነበረች፡፡ “ረጋቱ… ዼይሲቴ ጀላ ሂንባቱ!” (“ረጋቱን ሸሽተህ አታመልጣትም”) የተባለላት የሴት ኮማንደር!
ረጋቱ ትላንት ሞገደኛ የፋኖ መሪ ነበረች፡፡ እነሆ ስለዚህች ታሪካዊ ሴት ያለኝን ትዝታ ልጽፍ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን አንዳንድ የተሳሳቱ ምልከታዎችን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
በርካታ ሰዎች የኦነግ ሰራዊትን በፈሪነት ሲፈርጁት አያለሁ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የኦነግ ተዋጊዎችን ከጭካኔና ከጭፍጨፋ ጋር ያያይዟቸዋል፡፡ “በቢላዋ ሰው የሚያርዱ፣ ሰብዓዊነት ያልተፈጠረባቸው፣ የአመራር ብቃት የሌላቸው፣ የወደፊት ራዕይ ያልሰነቁ” ወዘተ የሚሉ ክሶችም ሲዥጎደጎዱ አያለሁ፡፡

ይህ ሁሉ ግን የፕሮፓጋንዳ ቅጥፈት ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የኦነግ ሰራዊት በጀግንነት ማነስና በወኔ ቢስነት የሚታማበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የሰራዊቱን የስልጠና ዘይቤና የውጊያ ቴክኒክ መተቸት ቢቻልም ከሰብዓዊነት ጎራ አውጥቶ አውሬ ማስመሰል በጣም ስህተት ነው፡፡ እርግጥ ኦነግ ችግር አለበት፡፡ ጉዞውም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሆኖም የዚህ ድርጅት ዋነኛ ችግር የነበረው አመራሩ ጋ ነው እንጂ ሰራዊቱ ጋ አልነበረም፡፡ አመራሩን በብቃት ማነስና በፖለቲካ ድክመት መገምገም ይቻላል፡፡ የድርጅቱን ዓላማና የፖለቲካ ስትራቴጂ መተቸትም ተገቢ ነው፡፡ ድርጅቱን ለወድቀት የዳረገውና አሁን ላለበት አሳዛኝ ሁኔታ የዳረገው ግን የሰራዊቱ ወኔ ማጣት እንዳልሆነ ሙሉ በሙሉ እመሰክራለሁ፡፡

ተዋጊዎቹም ቢሆን በጣም ሰብዓዊና ህዝባዊ አመለካከት ነው የነበራቸው፡፡ የበደኖና የአርባጉጉ ጭፍጨፋን የመሳሰሉ የፕሮፓጋንዳ ድርሰቶችን እያነበቡ የኦነግ ተዋጊዎችን መክሰስ ተገቢ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ እኔ እንዲህ የምላችሁ የኦነግ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ ስለረጋቱ የማወጋችሁም በታሪክ ጸሃፊነቴ ነው እንጂ በኦነግ ደጋፊነት አይደለም፡፡ ልማዴ ሆኖ ስለኢህአፓ፤ ስለኦነግ እና ሰለሻዕቢያ ማውራት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ወደፊትም ስለነዚህ ድርጅቶች ማውጋቱን እቀጥላለሁ፡፡

አሁን ወደ “ረጋቱ” እንሸጋገር፡፡

“ረጋቱ” የገበሬ ልጅ ናት፡፡ ትውልዷ በሀረርጌ ክፍለ ሀገር፣ በኦቦራ አውራጃ፣ በመልካበሎ ወረዳ ነው፡፡ እውነተኛ ስሟ አኢሻ አሕመድ ሲሆን ወደ ኦነግ ከገባች በኋላ “ረጋቱ ሮባ” የሚለው የትግል ስም ወጥቶላታል። ረጋቱ ሃያ ዓመት ሳይሞላት ነው ወደ ትግል ሜዳ የወጣችው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩትም ትግሉን የተቀላቀለችው በ1977 ዝነኛዋ “ጁኪ በሬንቶ” በተሰዋችበት ወቅት ነው፡፡ ረጋቱ ወደ ሜዳ ከወጣች በኋላ ልዩ ልዩ የውጊያ ጥበቦችን ተምራለች፡፡ በሶማሊያም የኮማንዶ ስልጠና ወስዳለች፡፡ ረጋቱ እስከ ደርግ የመጨረሻ ዓመታት በጫካ ቆይታለች፡፡ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሳትፋ ጀግንነቷን አስመስክራለች፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ኦነግ ከኢህአዴግ ጋር በጥምረት የሽግግር መንግሥት ሲመሰርት በፓለቲካ ካድሬነትና በአሰልጣኝነት ሰርታለች፡፡ ሆኖም በዚያ ዘመን ስሟ እምብዛም አይታወቅም፡፡ እርሷ ከነበረችበት የሀብሮ አውራጃ ክልል ውጪ ስለማንነቷም ሆነ ስለጀግንነቷ ብዙም አይወራም፡፡

ጊዜ አለፈ፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል “ያዝ-ለቀቅ” ሲል የነበረው የኢህአዴግና የኦነግ ግንኙነት ተበጠሰ፡፡ ወደ ማጎሪያ ካምፕ እንዲገባ ከተወሰነበት 30 ሺህ ከሚሆነው የኦነግ ሰራዊት መካከል የሚበዛው ክፍል ከካምፑ ርቆ ሳይሄድ ተማረከ (ኢህአዴግ ኦነግን አታሎ ወደ ካምፕ ካስገባ በኋላ ዙሪያ ገባውን ከቦ ይጠባበቅ ስለነበረ ነው ሰራዊቱ በቀላሉ የተማረከው)፡፡
የተወሰነው የኦነግ ሰራዊት ግን በኢህአዴግ ሳይማረክ ውጊያውን ቀጠለ፡፡ በተለይ በሀረርጌ፣ ባሌና ወለጋ የተካሄዱት አንዳንድ ውጊያዎች ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ መስዋእትነት ጠይቀዋል፡፡ በዚያ ወቅት የኦነጎች ትልቁ ችግር ብቃት ያላቸው የውጊያ ኮማንደሮች እጦት ነው፡፡ በርካታ ምንጮች እንደሚሉት ኢህአዴጎች ከተራ ተዋጊ ይልቅ በአመራር ደረጃ የነበሩትን ኮማንደሮች በማሳደዱ ላይ ነበር ያተኮሩት፡፡ በሌላ አገላለጽ በ1983 መጨረጫ ገደማ በኢህአፓ ሰራዊት ላይ የተጠቀሙትን ስልት ነው በሀረርጌና ባሌ የደገሙት፡፡
እናም ኦነግ በርካታ አዋጊዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥት አጥቷል፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ በኦነግ መንደር ያልተጠበቁ የጦር መሪዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ኦነግም የአመራር ድክመቱን በነርሱ ለማካካስ ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ በዚያ ወቅት ከሁሉም አዋጊዎች ይበልጥ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ የቻለችው “ረጋቱ” ነበረች፡፡

የ“ረጋቱ” በሀረርጌ ምድር መታየት ብዙዎችን ነበር ያስደነቀው፡፡ አንዳንዶች ከዓመት በፊት የተማረከችው “አያልነሽ” ስሟን ቀይራ ወደ ሀረርጌ የመጣች ነበር የመሰላቸው፡፡ በተለይ በአንድ ወር ውስጥ ከሃምሳ የማይበልጡ ተዋጊዎችን እያሰለፈች በርካታ የገጠር ከተሞችን ለመያዝ መቻሏ እጅግ በጣም አስደናቂ ነገር ሆኖ ነበር፡፡ ታዲያ ረጋቱ አደጋ ጥላ በአንድ ቦታ አትጠብቅም፡፡ እሁድ ሀርዲም ከተማ ከታየች ከሳምንት በኋላ 100 ኪሎሜትር ያህል ወደ ምስራቅ ተጉዛ ሌላ ከተማ ታጠቃለች፡፡ የጸጥታ ሀይሎች በመቻራ ከተማ ሲጠብቋት እርሷ ግን ወደ ሰሜን ተጉዛ በጭሮ (ዐሰበተፈሪ) አካባቢ አደጋ ትጥላለች፡፡ ከዚህ በላይ የሚገርመው ደግሞ የገጠሩን ክፍል እንዲያስተዳድሩ በኢህአዴግ የተሾሙ ሊቀመናብርት ለርሷ ትእዛዝ ተገዢ የመሆናቸው ነገር ነው፡፡ ሰዎቹ ቀን ቀን ከመንግሥት ጋር እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ማታ ማታ ግን በረጋቱ ለሚመራው መንግሥት ይሰራሉ፡፡ በአንድ ቀን ሁለት መንግሥት! በስፍራው የሚዘዋወር ባለመኪና የረጋቱን ትዕዛዝ መፈጸም ይጠበቅበታል፡፡ ለወታደሮቿ ኮቾሮ እና መድሃኒት እንዲያመጣ ከታዘዘ ይህንኑ መፈጸም አለበት፡፡ ባለመኪናው ለርሷ ትዕዛዝ ተገዥ አልሆንም ካለ ግን ከርሷ ግዛት እንዲወጣ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ በመኪናው የኢህአዴግን የጦር ሀይል የጫነ ሰው ወዮለት! ረጋቱ መኪናውን ከነባለቤቱ ድምጥማጡን ታጠፋዋለች፡፡

በ1986 አጋማሽ ነው፡፡ ጊዜው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ “ሀገራችን ሰላም ሆናለች፤ ጦርነት የለም፣ ኦነግ የሚባለው ድርጅት ከሀገር ጠፍቷል…” የሚል ይዘት ያለው መግለጫ የሰጡበት ወቅት ነው፡፡
የኦነግ መሪዎች የድርጅታቸው ህልውና ያላበቃ መሆኑን ለማሳየት ፈለጉ፡፡ አንድ አስደናቂ ኦፕሬሽን በመስራት የዓለምን ሚዲያ ወደነርሱ ለመመለስ ተመኙ፡፡ ነገር ግን ኦፕሬሽኑን የሚያካሄዱበትን መንገድ መተለም ቸገራቸው፡፡ ታዲያ ረጋቱን በቅርበት የሚያውቃት አንድ የድርጅቱ መሪ ይህንን ወሬ አደረሳት፡፡ ነገሩን የሰማችው ረጋቱ ለአለቃዋ “ይቻላል” የሚል ተስፋ ሰጠችው፡፡ ሆኖም ዝርዝር ነገሮችን በወቅቱ ከመግለጽ ተቆጠበች፡፡ ረጋቱ በነገሩ ላይ አሰበችበት፡፡ ሀሳቧን ከፍጻሜ የምታደርስበትን መንገድ ስታውጠነጥን አንድ ሰው ትዝ አላት፡፡

ማይክ ውድ ይባላል፡፡ የእንግሊዝ ዜጋ ነው፡፡ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን “ኬር ኢንተርናሽናል” የሚባለው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ተጠሪ ነው፡፡ ይህ ሰው ስፖርት በጣም ይወዳል፡፡ ከቢሮው ከወጣ በኋላ የቅርጫት ኳስና የመረብ ኳስ ጨዋታዎችን መጫወት ያስደስተዋል፡፡ ዘወትር ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት ደግሞ ከገለምሶ እስከ ገርቢ ጎባ ድረስ ይሮጣል (“ገርቢ ጎባ” በዚያ ዘመን ከገለምሶ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ 2.5 ኪሎሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ የገጠር መንደር ነው፡፡ አሁን ግን የከተማው አካል ሆኗል)፡፡ ማይክ ስራውን አክባሪ ነው፡፡

ከከተማው ህዝብ ጋር በጣም ይግባባል፡፡ ወደ ገጠር ብቻውን ቢወጣ እንኳ እርሱን የሚተናኮል ሰው አልነበረም፡፡ የጧት ጧት ሩጫው ደግሞ በማንም ዘንድ ታውቆለታል፡፡ ታዲያ ማይክ በአንድ ማክሰኞ የሩጫ ሀራራውን ለማድረስ ወደ ገርቢ ጎባ አቀና፡፡ እዚያ ከደረሰ በኋላ ግን አልተመለሰም፡፡ በኬር ግቢ አብረውት የሚኖሩት የስራ ባልደረቦቹ ቢጠብቁት የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ ጧት ጧት ወደሚሮጥበት አቅጣጫ ቢመለከቱ እርሱን የሚመስል ሰው አልታይ አላቸው፡፡ ነገሩ ግርምት የፈጠረባቸው ሰራተኞች ተሰባስበው ወደ ገርቢ ጎባ ነጎዱ፡፡ ሆኖም ማይክ ሊገኝ አልቻለም፡፡ በመንገዱ ያገኙትን ሰው እየጠያየቁ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ዘለቁ፡፡ ትርፉ ግን ድካም ሆኖ ቀረ፡፡ የማይክ መጥፋት ወሬ በከተማው ተዛመተ፡፡ ሰላማዊው ፈረንጅ ከመንገድ ተጠልፎ የተሰወረበት ምክንያት ለብዙዎች አልገባ አለ፡፡ ምሽት ላይ እንግሊዝ አንድ ዜጋዋ በሀረርጌ ክፍለሀገር ተጠልፎ እንደተወሰደባት ለዓለም ሚዲያ አሳወቀች፡፡ ቢቢሲና ቪኦኤ ወሬውን እየተቀባበሉ አራገቡት፡፡

ሶስት ቀናት አለፉ፡፡ ማይክን የበላ ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ሰውዬው በተጠለፈበት እለት አይተነዋል ያሉ ሰዎች በታጣቂዎች ተከቦ ወደ ቦኬ ወረዳ ሳይወሰድ እንዳልቀረ አወሩ፡፡ ቦኬ ከገለምሶ በስተምስራቅ ያለ ወረዳ ነው፡፡ ማይክ የተጠለፈው ግን በከተማዋ የደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ነው፡፡ ታዲያ ሰውየው እንዴት ተደርጎ ነው ወደ ምስራቅ የተወሰደው? ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን የሰዎቹ ግምት እውነት ሆኖ ተገኘ፡፡ ማይክ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ እጅግ በጣም ርቆ እንደተወሰደ ተረጋገጠ፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ከጠላፊዎቹ ጋር መደራደር ጀመረ፡፡ ጠላፊዎቹ ማይክ ውድን በሀረር ከተማ አቅራቢያ እንደሚለቁት ማረጋገጫ ሰጡ፡፡ ቢቢሲና ቪኦኤ “ማይክ የተጠለፈው በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት ነው” የሚል ዜና አስተላለፉ፡፡ የቀጠሮው ዕለት ደረሰ፡፡ ማይክ በተባለበት እለት ተለቆ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ ተወሰደ፡፡ የቢቢሲ ሬድዮ ስለጠለፋው ድራማ እንዲያብራራለት ጠየቀው፡፡ እርሱም “ከጠበቅኩት በላይ አስደሳች ጉዞ ነው የገጠመኝ” የሚል ቃል ተናገረ፡፡ በመጨረሻም ቢቢሲ የጠላፊውን ማንነት እንዲነግረው ጠየቀው፡፡
“ሴት ናት”
“ማን ትባላለች?”
“ረጋቱ”

ረጋቱ እስካሁን ካጫወትኳችሁ ሁሉ የሚበልጥ አንድ ኦፕሬሽን ሰርታለች፡፡ በወቅቱ ሶስት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች የነበሩበት ቡድን ከእዝ ሰንሰለቱ ተቆርጦ የሆነ ቦታ ተደብቆ ነበር፡፡ ከነዚያ አመራሮች መካከል ሁለቱ በወባ በሽታ ተጠቅተዋል። ረጋቱ እነዚያን ሰዎች ከአካባቢው ለማስወጣት መመራመር ያዘች፡፡ በወቅቱ የነበራት ሀይል አነስተኛ በመሆኑ ሰዎቹን በጦር ሀይል አሳጅባ ከአካባቢው መሸሽ እንደማይቻል አረጋግጣለች፡፡ በዚህ ላይ የጸጥታ ሀይሎች ስለሰዎቹ በስፍራው መኖር መረጃው ደርሷቸው ነበር ይባላል፡፡ ሆኖም ትክክለኛ ስፍራውን ማወቅ ተስኗቸዋል፡፡ ረጋቱ በነገሩ አሰበችበት፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባት አውጥታ አወረደች፡፡ ብዙ አማራጮችን ካየች በኋላ “መውሊድ ማድረግ አለብን” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰች፡፡ ከአምስት ያላነሱ በሬዎችን ጥሎ ህዝቡን ለድግስ በመጥራት መሪዎቹን በግርግሩ መሀል ማሳለፍ!
በርግጥም የመውሊድ በዓል ከጥንት ጀምሮ በስፍራው ይከበር ስለነበር በርሱ አስታክኮ መሪዎቹን ከአካባቢው ማራቅ ከሁሉም የቀለለው አማራጭ ነው፡፡ ደግሞም በዓሉ የሚከበርበት ምክንያት ለማንም ስለማይነገር ወሬው ለጸጥታ ሀይሎች የሚደርስበት እድል በጣም ጠባብ ነበር፡፡

ቀን ተቆረጠ፡፡ የበዓሉ ድግስ ተጀመረ፡፡ በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ወደ ስፍራው ነጎደ፡፡ ለህዝቡ ማስደሰቻ ሰንጋዎችና ፍየሎች ታረዱ፡፡ ዚክርና መንዙማ ተደረገ፡፡ ሀገር ምድሩ እየበላ መውሊድን በድምቀት አሳለፈ፡፡ ረጋቱም በእቅዷ መሰረት የኦነግ መሪዎችን በግርግሩ መሀል አሳለፈች፡፡ ይህኛው እቅድ በጊዜው በሰላም ቢፈጸምም የኋላ ኋላ አደገኛ ውጤቶችም ነበሩት፡፡ ለምሳሌ የጸጥታ ሀይሎች ከዓመት በኋላ ሚስጢሩን ስለደረሱበት ስለእቅዱ ምንም በማያውቀው የአካባቢው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴጎች ወደ ውጪ ሸሽቷል ብለው የገመቱት የኦነግ አመራር በሀገር ውስጥ መኖሩን ስላረጋገጡ ድርጅቱን አሳድዶ የማጥፋት እርምጃቸውን እንዲያፋጥኑ ቀስቅሶአቸዋል፡፡

ይህንን ሁሉ ገድል የፈጸመችው ሞገደኛዋ ኮማንደር ረጋቱ በህመም ተጠቃች፡፡ በሽታው ወደ ሞት አፋፍ ስለወሰዳት የምታደርገው ጠፋት፡፡ የኢህአዴግ ሰዎች መታመሟን ሲሰሙ እጇን ሰጥታ በሰላም እንድትመለስ ያባብሏት ጀመር፡፡ ሆኖም ረጋቱ የምትበገር አልሆነችም፤ እጇን ከመስጠት ይልቅ ሞትን እንደምትመርጥ በይፋ አሳወቀቻቸው፡፡ ይሁንና አንድ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር በድርጅቱ ውስጥ ታየ፡፡ ከትግሉ ሜዳ ርቀው በሚገኙ አመራሮች መካከል የፈነዳው ሽኩቻ ኦነግን ወደ አዙሪት ከተተው፡፡ ይባስ ብሎም አንድ የነበረው ድርጅት በሁለት ቦታ ተከፈለ፡፡ በዚህም ሳቢያም የጦር ሀይሉ ተበታተነ፡፡ ብቻዋን የቀረችው ረጋቱ የምትጨብጠውን አጣች፡፡ ለብዙ ዓመታት ጫካ የሰነበትችበት ዓላማ በመደነቃቀፉ ከልብ አዘነች፡፡ የቀራት ምርጫ እጅ መስጠት ነውና እጇን አስረከበች፡፡ ኢህአዴጎችም ከጎን ውጋታቸው እፎይ አሉ፡፡
ረጋቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመቻራ ከተማ ነዋሪ ነበረች፡፡ በእህልና ቡና ንግድ ላይ ተሰማርታ ነግዳለች፡፡ የዛሬ አራት አመት ገደማ ግን ከሀገር ተሰዳለች። “ረጋቱ… ዼይሲቴ ጀላ ሂንባቱ!” የተባለላት ሞገደኛ ሴት!!
ቸር ያቆየን!
—-
አፈንዲ ሙተቂ
(October 23/2013)


Faajjii Dhugaa