ምክረ ሃሳቡ የአይሁድ ወይስ የሐዋርያት?

ምክረ ሃሳቡ የአይሁድ ወይስ የሐዋርያት?
 
የኦሮሚያ ቤተክህነትን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በ18/02/2012 ዓ.ም ያጸደቀውን ምክረ ሀሳብ በተመለከተ ያለኝ አስተያየት እነሆ። ጽሑፉን በ7 ክፍሎች ያሰናዳሁ ሲሆን ቀሪዎቹን የመጨረሻ ክፍሎች ነገ አቀርብላችኋለሁ።
 
ክፍል 1
 
የምክረ ሃሳቡ ርዕስ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያንና ራሳቸውን የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ ብሎ በመሰየም ሲንቀሳቀሱ በነበሩት የቤተክርስቲያን ልጆች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የሃሳብ ልዩነትና ውዝግብ ለማቀራረብ የተደረገ ሽምግልና ስምምነት ዝርዝር የአፈጻጸም ምክረ ሃሳብ” ይላል። የተዘጋጀው መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው። የምክረ ሃሳቡ አዘጋጆች በሽምግልና ጉዳዩን ሊፈቱ ጥረት በማድረግ ላይ የነበሩ አካላት ናቸው። ስማቸው በምክረ ሀሳቡ ላይ ተዘርዝሮአልና አልድገመው። ይህ ምክረ ሀሳብ አስቀድሞ ለቋሚ ሲኖዶሱ ቀርቦ የጸደቀ ነው። በትላንትናው እለት በንባብ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቀርቦ ጸደቀ የተባለለት ነው፣ ምክረ ሀሳቡ።
 
ምክረ ሃሳቡ ለቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ተነበበ እንጂ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት በዝርዝር አልተወያዩበትም። እርግጥ ነው በአምስት አባቶች ሀሳብ ተሰጥቶበታል። ይሁን እንጂ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ በቂ ማብራሪያ ተሰጥቶ በቂ ውይይት አልተደረገበትም። ያለምንም ድምጽ ቆጠራ የቤተክርስቲያኒቱን ሕግ በጣሰ መልኩ በጭብጨባ ብቻ የጸደቀ ነው። ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌሌለው የውሳኔ መንገድ ነው።
እኛ የጠየቅነው ጥያቄ ግልጽ ነው። የኦሮሚያ ቤተክህነት መዋቅር ነው። ይህ በምድርም ሆነ በቤተክርስቲያን ሕግ እንከን የሌለው ጥያቄ ነው። ታዲያ ምን ተፈርቶ ነው ድምጽ በአግባቡ ሳይቆጠር እና በእርግጥም የምልዓተ ጉባዔው አባላት ፍላጎት መሆኑ ሳይረጋገጥ ጭብጨባ ተሰምቶ ምክረ ሀሳቡ የሚጸድቀው? በጣም ይገርማል እኮ! በዚህ ሲኖዶስ አልነበረ እንዴ የኦሮሚያ ቤተክህነትን በተመለከተ ዋልታ ረገጥ እይታዎች ሲስተናገዱ የነበሩት? ቢያንስ እነዚህ ዋልታ ረገጥ እይታዎችን የሚያስማማ ምን እንደተገኘ ለመረዳት ሰፊ ውይይትና ሕጋዊ የሆነ የድምጽ ቆጠራ አያስፈልግም ነበር?
 
ክፍል 2
 
የምክረ ሃሳቡን ርዕስ ስናጤነው ግን በእውነት፣ በእኩልተኝነት ስሜት እና በተመጣጠነ የመደራደር አቅም በኦሮሚያ ቤተክህነትና በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል ስምምነት እንዳልተፈጠረ የሚያሳብቅ ነገር ታገኛላችሁ። ርዕሱን ቃል በቃል ላስፍርላችሁ:
“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ራሳቸውን የኦሮሚያ ቤተክህነት ኮሚቴ ብለው በመሰየም ሲንቀሳቀሱ በነበሩት” መካከል የተደረገ የሽምግልና ስምምነት እንደሆነ ይገልጻል። አንደኛ የኮሚቴው ስም በምክረ ሀሳቡ ላይ የተገለጸው አይደለም። የኮሚቴው ስም “የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ” ይባላል። ሁለተኛ ኮሚቴው ራሱን እንዲህ ብሎ መሰየሙ ላይ ያተኮረ ይመስላል። ዋነኛው ነገር ግን የኮሚቴው እራሱን እንዲህ ብሎ መሰየም አለመሰየም አይደለም። ዋነኛው ነገር የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ መሬት የወረደ እውነት የመሆኑ ጉዳይ ነው። ርዕሱ ይህን መቀበል ባለመፈለጉ ምክንያትም ይሁን በዝንጋዔ ልቡና ወይም ባለማስተዋል “ብለው በመሰየም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ” የሚለውን ሐረግ ጨምሮበታል።
 
ሦስተኛው እና ዋነኛው ርዕሱ በኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን እና በኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ መካከል የተፈጠረውን የሃሳብ ልዩነት እና ውዝግብ ለማቀራረብ የተደረገ ሽምግልና ምክረ ሀሳብ እንደሆነ ይናገራል። ውዝግብ እንዴት እንደሚቀራረብ ለእኔ ግልጽ ባይሆንም ዋነኛው ነጥብ ግን በኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴው እና በሲኖዶስ መካከል ምንም ዓይነት ውዝግብ ሳይኖር ምክረ ሀሳቡ ያልነበረን ውዝግብ ለመፍታት መሞከሩ ነው።
 
የኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄውን ከጫረበት ጊዜ ጀምሮ ስለ አንድ ፓትርያርክ፣ ስለ አንድ ሲኖዶስ እና ስለ አንዲት ቤተክርስቲያን ከመስበክ እና ከመሞገት የታቀበበት ጊዜ አልነበረም። የኦሮሚያ ቤተክህነት መዋቅርንም የጠየቀው በነዚሁ አንድ ቅዱሳን ፓትርያርክ፣ ሲኖዶስ እና ቤተክርስያን ስር ነው። ውዝግቡ የተፈጠረው የቤተክርስቲያንን እጅ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊጠመዝዙ በሞከሩ የቤተመቅደሱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ነጋዴዎች እና በኮሚቴው መካከል ነው። ስለዚህ በቤተክርስቲያን ከለላ ፖለቲከኞቹና ቤተክርስቲያንን እንጀራ መቁረሻ ያደረጉ ነጋዴዎች ከኮሚቴው ጋር የፈጠሩትን እሰጥ አገባ ከቤተክርስቲያን የተጣላን ለማስመሰል የተኬደበት ሂደት ስህተት ነው። የዚህ አገላለጽ ዓላማው የቀድሞውን የኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄ ፖለቲካዊ፣ የእስልምናና የፕሮቴስታንንትን ጫና በቤተክርስቲያን ላይ ለማንበር እንደታሰበ ተደርጎ ሲተረጎምበት የነበረውን የተረፈ አይሁድን ድምዳሜ ማስረገጥ ነው።
 
ክፍል 3
 
ወደ ይዘቱ ዘልቀን በምክረ ሀሳቡ ተ.ቁ.1 የተገለጸውን ስንመለከት የእስከዛሬውን የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ ለዚህ ዓላማ ሲጋደሉ የነበሩ ምዕመናን እንዲሁም ሕዝቦችን ድካም በመና (በዜሮ) ያባዛ ሐረግ እናገኛለን። በመጀመሪያው ሐረግ አምና በዚህን ጊዜ የተወሰነን ውሳኔ ያስታውስና ለጥቆም አምና በሲኖዶሱ የተሰጠው ውሳኔ ኮሚቴው ይዞት የተነሳውን ጥያቄ በአብዛኛው የመለሰ እንደሆነና ዘንድሮ ኮሚቴው እንደተቀበለው ያረጋግጣል።
 
ዘይገርም ነው እኮ! አምና የተወሰነው ውሳኔ ጥያቄያችንን በአብዛኛው ከመለሰ አመቱን ሙሉ እስከ ደም ጠብታ እና እስከ ሕይወት ሕቅታ ጥያቄያችን እንዲመለስ መታገሉ ለምን አስፈለገ? ለምንስ የብዙ አገልጋዮች መሰደድ፣ ከስራ መሰናበት፣ መታሰር እና የማኅበራዊ ሕይወት መቃወስ አስፈለገ? ለምንስ ያን ሁሉ የፈሪሳውያን ስድብ ወቀሳ፣ ዛቻ እና ከሰሳ ማስተናገድ አስፈለገ? ለምንስ በቅርቡ በሰበታ የአንድን ካሕን ሕይወት ማጣት አስፈለገ?
 
እሺ ይህን ውሳኔ ዓመቱን ሙሉ እነዚህን ሁሉ ዋጋ ከፍለን ከምንቀበል አምና እንደተወሰነ ወዲያውኑ መቀበል አይቻልም ነበር? ወይም ደግሞ አምና ያልተገለጠልን ዘንድሮ የተገለጠልን ምን እውነት አለ?
ይህ እንግዲህ በእውነት ምክሩ ምክረ አይሁድ ነው ወይስ ምክረ ሐዋርያት ብለን እንድንጠይቅ ብርታት ይሰጠናል?
 
ክፍል 4
 
እናም ምክረ ሀሳቡ የአምናውን የኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄ ውድቅ የተደረገበትን ውሳኔ ተቀብለናል ይላል። ተወስኖአል ብሎ የሚያስታውሰን “የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ልጆች ምዕመናን በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ እንዲቀድሱ እና በአገልግሎት እጦት ከእናት ቤተክርስቲያናቸው የወጡ እንዲመለሱ በቤተክርስቲያናቸው ያሉት የበለጠ እንዲጠናከሩ” የሚለውን ነው። ይህ ግን በአምና የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ብቻ የተወሰነ አይደለም። አስቀድሞም የጋራ ግንዛቤ ተይዞበት ትክክለኛ የሆነ ሐዋርያ ሲያከናውነው ተረፈ አይሁዶች ሲያደናቅፉት የነበረ ነው። የዚህ ዓይነት ክፍተት እንዳይፈጠር እና የተረፈ አይሁድን ሴራ ወደየምኩራቦቻቸው ለመመለስ ነው የኦሮሚያ ቤተክህነት የሚባል መዋቅርም ያስፈልጋል የተባለው።
ስለዚህ ዋነኛው ጥያቄ የመዋቅር ጥያቄ ነው። የመዋቅሩ ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ አገልለግሎቱ በተሟላ መልኩ ይሰጣል የሚል እምነት ነው ያለን። ስለዚህ የመዋቅር ጥያቄውን ደቃቃ አድርጎ መምከርና ከዚህ ውጭ ላለው ጥያቄ የአንበሳ ድርሻ መስጠት ተገቢ አይደለም። የጠየቅነውን ዳኝነት የምንረሳ ቸልተኛ ተሟጋችም ስላልሆንን አብዛኛው ጥያቄ እንደተመለሰ አድርጎ ግርታ መፍጠርም ምንጭ ካልሆነ ትልቁን የአbbaያ ወንዝ አያሻግርም።
 
ምክረ ሀሳቡ ይቀጥላል። በተ.ቁ.1.1. ላይ አጥኚ ቡድን እንዲቋቋም ይጠቁማል። ይህ አጥኚ ቡድን ምን እንደሚያጠና ግን አይታወቅም። የተጠየቀው የኦሮሚያ ቤተክህነት መዋቅር ነው። ይህ አያከራክርም። ታዲያ ምክረ ሀሳቡ አጥኚ ቡድኑ የኦሮሚያ ቤተክነትን የመዋቅር ጥያቄ እንደሚያጠና ለመግለጽ እንዴት ተሳነው?
 
ክፍል 5
 
በተ.ቁ.2 ስር ደግሞ የተነሱ ጥያቄዎችን በአንዲት ቤተክርስቲያን ስር ሆኖ ለመመለስ እንዲቻል ተብሎ በተ.ቁ. 2.1 እና 2.2. ስር ያሉ ውሳኔዎች እንደተወሰኑ መግቢያው ያስረዳል። ምን ማለት ነው? የኦሮሚያ ቤተክህነት ይቀቋም ስንል ከአንዲት ቤተክርስቲያን ስር ወጥተን ነው እንዴ? ደግመን ደጋግመን በአንድ ሲኖዶስ፣ በአንድ ፓትርያርክ እና በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን ብለን ስንምል ስንገዘት ነበር እኮ። ምነው ታዲያ ምክረ ሀሳቡ ከቤተክርስቲያን የተለዩትን የሚመልስ ዓይነት ሆኖ ተደራጀ? ወይስ ጥቂት አባቶች በፖለቲካ እጃቸው ተጠምዝዞ ሥልጣነ ክህነትን ለመያዝ እና ከአግልግሎት ለማገድ ያደረጉትን ሙከራ እውቅና እየሰጠ ነው? ወይስ ፖለቲከኛ እና ሆድ አደር ነጋዴዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ያስተጋቡትን ቧልት እያስረገጠ ነው?
 
በዚህ በተሳሳተ ዳራ (background) መሠረት በተ.ቁ. 2.1 እና በተ.ቁ.2.2. ላይ ለኦሮሚያ ቤተክህነት አባላት ምድብ ይሰጣል። ገራሚ ነው። እኛ የምደባ ጥያቄ አንስተናል እንዴ? እኛ እኮ ያነሳነው የኦሮሚያ ቤተክሀነት የመዋቅር ጥያቄ ነው ያነሳነው? ለምንድነው ታዲያ የኦሮሚያ ቤተክህነትን ሰብሳቢ፣ ም/ሰብሳቢ እና ም/ፀሐፊ እና ሂሳብ ክፍል መመደብ ያስፈለገው። ግልጽ ነው። የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴን ለማፍረስ። የኦሮሚያን ቤተክህነት አመራሮች ከዚህ ቀደም ሲኖዶሱን ሲያውክ በነበረ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የእዝ ሠንሠለት ስር ለማስገባት። ይህ ካልሆነ የኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄ የመዋቅር ጥያቄ እንደሆነ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ካህናቱን በመመደብ ጥያቄውን ለማስቀየስ እና ለማኮላሸት የተኬደው ሂደት ይገርማል። በእርግጠኝነት ግን አይሰምርም።
 
በተ.ቁ.2.2. ላይ ደግሞ ሌሎች የኮሚቴውን አባላት የአገልግሎት ፍላጎት ያሳውቀናል። ይኸውም በአጥኚ ቡድን በሌሎች የቤተክርስቲያን ስራዎች ላይ እንደሆነ ያሳውቀናል። ስለ እነዚህስ ምድብ ማን ጠየቀ? ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ይህ ምክረ ሀሳብ አያስፈልግም። ባለን አቅምና አጋጣሚ ስናገለግል ነበርን። እያገለገልንም ነው። እንዳናገለግልም በሕጋዊ መንገድ የከለከለን ኃይል የለም። ሊከልክለን የሚችልም ኃይል ከሰማይ በታች የለም። ስለዚህ ከካህናቱ ውጭ ላሉትም አገልጋዮች የስራ መደብ እንዲሰጥ ባልተጠየቀበት ሁኔታ ለኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄ የእኛን ምድብ እንደ መፍትሄ ማቅረብ ጥያቄውን ለማስቀየስ እና ኮሚቴውን ለማፍረስ ነው። ጥያቄውም አይቀየስም፣ የሕዝብን እና የምዕመናንን ዓላማ ያነገበም የኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄም አይኮላሽም።
 
ክፍል 6
 
በምክረ ሀሳቡ ተ.ቁ. 3 ላይ የተገለጸው መንጋ ከመሰብሰብ ይልቅ ንብረት መሰብሰብ ላይ ያተኮረ ነው። ኮሚቴው ለአገልግሎቱ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ንብረቶች የቤተ ክህነት ንብረት እንዲሆኑ ምክር ይለግሳል። የቤተ ክህነት ቤተክህነት የኦሮሚያ ቤተክህነትስ ቤተክህነት አይደለም እንዴ? ወይስ የኦሮሚያ የሚለው ስያሜ ነው ችግር የሆነው? የኦሮሚያ ቤተክህነትን በአግባቡ አደራጅቶ ንብረቱንም ሆነ አገልግሎቱን ለእርሱ ማስረከብ አይሻልም ነበር? ይህ ንብረት በኦሮሚያ ቤተክህነት እጅም ቢቀጥል ለቤተክርስቲያን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ንብረቱን መሰብሰብ የተፈለገው ኦሮሚያ ቤተክህነትን አቅም ለመንሳትና ንብረቱንም ሆነ አባላቱን ቤተክርስቲያንን የፖለቲካና የእንጀራ መቁረሻ ንግድ ባደረጉአት ስውር ኃይሎች መዳፍ ስር እንዲወድቁ ለማድረግ ነው።
 
በተ.ቁ. 3.1. ስር OCN tv የቤተክርስቲያን ልሳን ሆኖ እንደሚቀጥል ይመክራል። ይኼ አከራካሪ አይደለም። ሲጀመርም የቤተክርስቲያን ልሳን ነው። ግን እንደዚያ ሆኖ እንዲቀጥል ዋስትናው ምንድነው? የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴው ከፈረሰ በOCN tv ለሕዝቡ ተደራሽ አገልግሎትን የሚሰጠው ማነው? ማን ይመራዋል? በቤተክርስቲያን የተሰገሰጉ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅመኞች? ቦርዱስ አባላቱ አብዛኞቹ ወደ ሌላ የአገልግሎት ዘርፍ እንዲመደቡ በተደረገበት ሁኔታ OCN በትክክል ለተባለው ዓላማ ይውላል ማለት ዘበት ነው።
በተ.ቁ.3.2.ደግሞ የኦሮሚያ ቤተክህነት ማኅተም ጥቅም ላይ መዋሉ እንደሚቆም ያረዳናል። ታዲያ የኮሚቴው ሕልውና የቱ ጋ ነው? ያለ ማኅተም በምን መልኩ ነው ስራዎችን መስራት የሚቻለው?
 
ክፍል 7
 
ምክረ ሀሳቡ በተ.ቁ.4. ላይ ስምምነቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲጸድቅ ሠላም መውረዱንና ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጫ እንደሚሰጥ ያትታል። መግለጫው የሚያስፈልገው ደግሞ ስለ ቤተክርስቲያን አንድነት ሲጨነቅና ሲጸልይ ለኖረው ምዕመን ነው።
ስለ ቤተክርስቲያን አንድነት መጸለይና መጨነቅ ተገቢ ቢሆንም እንዲሁም ስለዚህ ጉዳይ ለተጨነቁ ምዕመናን ክብር ቢኖረንም የኦሮሚያ ቤተክህነት ግን የቤተክርስቲያንን አንድነት አልከፈለም። እንዲያውም የቤተክርስቲያንን ተደራሽነት በኦሮሚያ ቤተክህነት መዋቅር በኩል በማረጋገጥ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለማስቀጠል ትልቅ ሚና ለመጫወት የተደራጀ ነው። ስለዚህ እርቅና ሠላም መውረዱን መግለጹ ጥሩ ሆኖ የኦሮሚያ ቤተክህነትን በአፍራሽነት በመፈረጅ የሚከናወነው የእርቅና የሠላም እወጃ የይስሙላ እና ፋይዳ ቢስ ነው።
በተ.ቁ.4.1. ስር እርቁ ያለውን ችግር በአንዲት ቤተክርስቲያን ስር ሆኖ መፍታት እንደሚቻል ስለተግባባን የተፈጸመ እንደሆነ መገለጽ እንዳለበት ተጠቁሞአል። ቆይ ግን የኦሮሚያ ቤተክህነት የመዋቅር ጥያቄ ማቅረብ ከቤተክርስቲያን መውጣት ነው እንዴ? ኦሮሚያ የሚለው ስያሜ ካልጸነነን በስተቀር የቤተክህነት መዋቅር እንደሆን ከጠቅላይ እስከ ወረዳ የተዘረጋ ነው። ታዲያ ምንድነው የመዋቅርን ጥያቄ ከቤተክርስቲያን ከመውጣት ጋር የሚያስተካክለው?
 
በተ.ቁ. 4.2. ስር የሠላምና የእርቁ እወጃ የቤተክርስቲያንን አሸናፊነት እንጂ የራስን አሸናፊነት ማንጸባረቅ እንደሌለበት ይገልጻል። ግን እኮ የዚህ ዓይነቱ እርቅ የጥቂት የፖለቲካ ቡድኖችን እንጂ የቤተክርስቲያንን አሸናፊነት አያሳይም። ምክንያቱም ቤተክርስቲያን የምታሸንፈው የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ ሲፈርስ፣ ማኀተሙ ሲታገድ ንብረቱ ሲዘረፍ እና የአደራጅ ኮሚቴውን ድካም እና ከበስተጀርባው ያለውን ሰፊ ሕዝብ ምዕመናን ድካም ጥላሸት በመቀባት አይደለም። ቤተክርስቲያን የምታሸንፈው የኦሮሚያ ቤተክተህነትን በማደራጀት ለሁሉም የአካልክፍሎቿ ተገቢውን ምላሽ ስትሰጥ ነው።
 
በተ.ቁ. 4.7. ስር የኮሚቴው አባላት ከአሁጉራነ ስብከቶች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ዕቅድ እንደሚያወጡ ይነግረናል። ይህም በግልጽ የኮሚቴውን መፍረስ ያረዳናል። ምክንያቱም በዚህ ሀሳብ መሠረት እቅዱን ከአባቶች ጋር በመሆን የሚያወጣው ኮሚቴው እንደ ተቋም ሳይሆን የኮሚቴው አባላት በግለሰብ ደረጃ የሚያወጡት ነው። በዚህ መሠረት ምክረ ሀሳቡ የኦሮሚያ ቤተክህነትን ጉዳይ ከተቋም እና ከሕዝብ አውርዶ የጥቂት ግለሰቦች አጀንዳ አድርጎታል።
.
.
.
ይቀጥላል…