ምን ያህል ሱማሌዎች በፌዴራል መ-ቤቶች ተቀጥረው ይሰራሉ?

ምን ያህል ሱማሌዎች በፌዴራል መ-ቤቶች ተቀጥረው ይሰራሉ?

የዝህ ጥያቄ መልሱ በጣም ጥቂት ወይም ደርዘን የማይሞሉ ተብሎ ሊነገር ይችላል፡፡በአንዳንድ መስርያ ቤቶች ለመድሃኒት ቢፈለጉ አይገኙም፡፡ አስቡት ከአገሪቱ ከሚኖሩት ብሄር ብሄረሰቦች በሕዝብ ብዛት 3ኛው ነው፤ ከኦሮሞና ከአማራ በመቀጠል ማለት ነው፡፡ በመሬት ስፋት ደግሞ ከኦሮሚያ በመቀጠል 2ኛው ነው፡፡
ለምን ይህ ታላቅ ሕዝብ ጥቅት እንኳ ሰዎቹን በፌዴራል መስሪያ ቤቶች እንድቀጠሩለት አልተደረገም ሲባል ከሚቀርቡት ምክንያቶች የሚጠቀሱት፡-
• አማሪኛ ቋንቋ መናገር አይችሉም፤
• ከክልላቸው ውጭ መስራት አይፈልጉም ስለዝህ ውድድር ውስጥ አይገቡም፤
• አቅማቸው ውስን ነው፤
• ኢትዮጵያዊነታቸው ያጠራጥረናል የሚሉ ናቸው፡፡

እነዝህ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች አንዳቸውም ውሃ አይቋጥሩም፡፡ ይልቁንም ለዝህ ታላቅ ሕዝብ ንቀትን ያመላክታሉ፡፡ ዛሬ ብዙ ሱማሌዎች መኖሪያቸውን አድስ አበባ አድርገዋል፡፡ አማሪኛን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ (አማሪኛ መናገር የዕውቀት መለኪያ ባይሆንም እንኳ)፡፡ በትምህርት ደረጃ ከማንም አይተናነሱም፡፡ በዝያ ላይ በሱማሌ ማንነታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ ምንም አይነት ቅራኔ የለባቸውም፤ በአጭሩ በኢትዮጵያዊነታቸው ይኮራሉ!

ለምን አልተቀጠሩም ሲባል ሚዛን የሚደፋው ሐሳብ ሁለት ነው፡፡
1. የተቋም ተፅዕኖ መኖር (በመንግስት ተቋሞች ሱማሌዎች ሥራ እንዳያገኙ ብዙ ማነቆዎችና መሰናክሎች ተቀምጠዋል)
2. የአመለካከት ችግር፡- አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለሱማሌዎች ያለው አመለካከት ሸውራራ ነው ቢባል ከእውነት ብዙም አይርቅም፡፡ ስለሱማሌ ሲነሳ ሁሉግዜ የሚታየው አገሩ እንጂ ሕዝቡ አይደለም፡፡ስለዝኛው ሱማሌ ሲነሳ በአዕምሮው የሚመጣበት የመጀመሪያ ስዕል መቋድሾ ነው፡፡

አድሱ የፕሬዝደንት ሙስጠፋ አስተዳደር ይህን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመስራት ከታች በተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች የሰማሌዎች ተሳትፎ እንዲጨምር ከፍተኛ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡መስሪያ ቤቶቹም፡-
1. ሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶች (ጠ/ሚ ቢሮ፣ ውጭ ጉዳይ፣ ፌዴራል ጉዳዮች፣ ግብርና፣ ገንዘብ፣ገቢዎች ውሃ ልማት ወዘተረፈ)
2. ቴሌኮሙኒኬሽን
3. መብራት ኃይል
4. ንግድ ባንክና ብሄራዊ ባንክ
5. አየር መንገድ
6. ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት
7. የደህንነት መሥሪያ ቤት
8. ኢትዮጵያ በውጭ ያላት ኤምባሲዎች
9. ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት
የሱማሌ ሕዝብ ከፌዴራል ቅጥር ምንም የተጠቀመው ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ አገራችሁ ናት ለኢትዮጵያም አታገለግሉም ማለት የሚቻል ስላልሆነ ሱማሌዎች በስፋት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ውስጥ በመግባት አገራቸውን እንድያገለግሉ መንግስት ኦዎንታዊ እርምጃዎች ወስዶ መንቀሳቀስ መቻል አለበት! ካለዝያ ራሳችንን በስስተሙ ውስጥ ካላየነው እንዴት ኢትዮጵያዊነታችን ሊሰርፅብን ይችላል፡፡ ጥያቄው የፍትህና የእኩልነት በመሆኑ መንግስትና የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥተውት ሊንቀሳቀሱበት ግድ ይላቸዋል!

Via Rajo