ምርጫ 2013ን አስመለክቶ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግለጫ

 

ምርጫ 2013ን አስመለክቶ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግለጫ

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንደሚካሄድ በመንግስትና በምርጫ ቦርድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ ኦፌኮ እያየ እና እየሰማ ነው፡፡ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እንዲገነባ ከምስረታው ጀምሮ በምርጫ ውስጥ ሲሳተፍ የቆየው ፓርቲያችን (ኦፌኮ) ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታትና በላይ በሠላማዊ መንገድ እየታገለ ለ6ኛ ጊዜ በ2012 ሊካሄድ ታቅዶ ለነበረው አገራዊ ምርጫም ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ እያለን ምርጫው መተላለፉ ይታወሳል፡፡ አሁንም በ2013 እንዲደረግ በተያዘው ዕቅድ መሠረት በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለንም ይታወቃል፡፡
ነገር ግን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ስናሳውቅ እንደቆየነው ሁሉ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ታዛቢ፣ ተወዳዳሪና አስተባባሪ ሊሆኑ የሚችሉ አመራርና አባሎቻችን ታስረውና ከማዕከላዊ ጽ/ቤት ውጭ ያሉ አብዛኛው ቢሮዎቻችን ተዘግተው ባሉበት ሁኔታ ውስጥ በምርጫው ለመሳተፍ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ የተሳካ ብሔራዊ መግባባት ላይ ተደርሶ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት ባለው ሁኔታ እንዲደረግና በአገራችን ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፤
1. የታሰሩ አመራሮችና አባሎቻችን በሙሉ እንዲፈቱ፣
2. በመንግስት ኃይሎች የተዘጉ ጽ/ቤቶቻችን እንዲከፈቱ፣
3. በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታችን ተከብሮ የምርጫው ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር እንዲፈጠር እንጠይቃለን፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ፊንፊኔ፤ ሕዳር 30/2013 ዓም

ትኩረት ያልተሰጠው የሞሳድ ኦፐሬሽን!

ሰሞኑን እስራኤል ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ከጎንደር አካባቢ “ቤተሰብ ማገናኘት” በሚል ፕሮጀክት የማጓጓዝ “ኦፐሬሽን ሮክ ኦፍ እስራኤል” በሚል የኮድ ስም አከናውናለች። ሂደቱ ሞሳድ በትውለደ ኢትዮጵያውያን መሪነት ኢትዮጵያን እንዲቆጣጠር የተደረገበተ ነበር። ለዚህ ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የእስራኤል የስደተኞች ሚኒስትርና ሌላ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሞሳድ አባል አድስ አበባ መሰነበታቸው ይታወቃል።
መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግራይ ውስጥ ይካሄድ በነበረው የጦርነት ሂደት ላይ አይኑም፣ ጀሮውም፣ ቀልቡም ተጠምዶ በነበረበት ወቅት እስራኤል ኮሽታ ሳታሰማ የተፈለገውን ኦፐሬሽን አጠናቃለች። ሞሳድ ማለት እንዲህ ነው ሌላ ምስጢር የለውም። አንተ የሆነ ነገር ላይ ስታንጋጥጥ ብብትህ ስር ገብቶ ሆድ ዕቃህን አራግፎህ ይሄዳል።
 
በ1983 ዓም በዚያ የደርግ የመጨረሻ የጭንቅ ቀናት ከፍተኛ ባለስልጣናትን(እነካሳ ከበደን) በቃሬዛ ላይ አስተኝቶ ወደ እስራኤል ያጓጓዘው ሞሳድ ዛሬም ተመሳሳዩን ስላለመስራቱ ማረጋገጫ የለም። ካልጠፋ ጊዜ ለምን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ በምትገኝበት ወቅት እስራኤል ይህን ኦፐሬሽን ማድረግ አስፈለጋት? የኢትዮጵያ መንግስትስ ለምን ፈቀደ?
ለማንኛውም የሆነ ነገር ተፈፅሟል። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እጅ ይኖርበትም ይሆናል። “የህወሓት ባለስልጣናት ተያዙ፣ አመለጡ” የሚለው የተሳከረ መረጃም መንጋውን እያወዛገበ ቀጥሏል።
ቀኑ ሲደርስ ጉዳዩ ከተዓምረኛው የሞሳድ ገድሎች እንደ አንዱ ይተረክልናል። መንጋው ያኔ እጁን አገጩ ላይ ጭኖ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ አይኑ እያየ የተፈፀመውን ታሪክ “አጀብ ነው” እያለ እንደ አዲስ ያዳምጣል።
Via: Dan Dimension