ሚሊተሪዝም ለኢትዮጵያ?አሁን አሁን እያስተዋልን ያለነው አብይ አህመድ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ዱካ እየተከተለ መምጣቱን ነው።

ሚሊተሪዝም ለኢትዮጵያ?

አሁን አሁን እያስተዋልን ያለነው አብይ አህመድ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ዱካ እየተከተለ መምጣቱን ነው። “ታፍራና ተከብራ የሚትኖር ኢትዮጵያ” የተሰኘውን የመንግሥቱ አሮጌ መዝሙር እየሸመደደ ነው። የደርጉን ዘመን የቴፕ ክር አቧራውን እያራገፈ ሲያደምጥ የሚያድር ይመስላል።

በቅርቡ በአንድ ጥቂት ሰዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ 60,000 የሪፓብሊካን ጦር ፈረንሳይና እንግሊዝ ሊያሰለጥኑለት ቃል እንደገቡለት ተናግሯል። የጦረኝነት መንፈስ ሳይሰፍርበት አልቀረም። ግን ለምን? የትስ ያደርሰዋል?
ጦርነቱን የጀመረው ደግሞ ከኦሮሞ ጋር ነው። በቀደምለት የ4 ቢሊዮን ዩሮ የጦር መሳሪያ ግዥ ከፈረንሳይ ጋር ተከናውኖ መሣሪያዎች ሲጓጓዙ የሚያሳይ ዜናም በዚሁ ሶሻል ሚዲያ ላይ አንብበናል።

እኔ ይኸ ሰውዬ እልም ባለ ቅዠት ውስጥ የተዘፈቀ ይመስለኛል። እንኳንስ በቅራኔዎችና ራሱ በፈጠራቸው ባላንጣዎች እየተናጠ ያለ ገና ያልጠና መንግስት ይዞ፣ እንኳንስና መሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሁለት ዋና ዋና ክልሎች (በትግራይና በአማራ) ላይ ምንም ቁጥጥር ሳይኖረው፣ እንኳንስና ሙሉ በሙሉ በራሱ ቤዝ በኦሮሚያ ተተፍቶ እንደ መንግሥት የመንግስቱ ኃይለማርያምም ጠንካራ ሚሊተሪ ቢገነባ የአብይ መንግስት የርስ በርስ ጦርነቱን አያሸንፍም።

መንግሥቱ ኃይለማርያም በ1983 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መጥቶ ተማሪዎችን ወደ ቢላቴ የወታደር ማሰልጠኛ እንዲገቡ በቀሰቀሰ ጊዜ እንባ እየተናነቀው የተናገረውን አስታውሳለሁ።”ጓዶች” አለ መንግሥቱ፣ “ጓዶች፣ ከሶማሊያ ጋር ያካሄድነው ጦርነት ሠርጋችን ነበር። ከውጭ ወራሪ ጋር ስትዋጋ ጠላትህን ታውቃለህ። ወረዳውን፣ ቀጠናውን፣ ርቀቱን ትለያለህ። የርስበርስ ጦርነት ግን ውስብስብና ፈታኝ ነው” ጥቂቱን ብቻ ነው እዚህ የጠቀስኩት።

እናም አብይ አህመድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ጥልቀትና ወርዱን አልተረዳም ማለት ይቻላል። የርስ በርስ ጦርነት ማለት ምን እንደሆነ በወጉ አላጤነውም። እነሆ በሁለት ሳምንት እጨርሰዋለሁ ብሎ የፖለቲካ ጥያቄ ባነሱት አማፅያን ላይ የከፈተው ጦርነት ብዙ መዘዝ ይዞ ወደ ሁለት ዓመት እየቀረበ ነው። በመሣሪያ ጋጋታ፣ በኮማንድ ፖስት፣ በማሰር በመግደል፣ በማታለል፣ በመዋሸት ሊፈታው እየተንገታገተ ነው። እርሱን አካሄድማ በጉልበትም፣ በእውቀትም ከርሱ የተሻሉቱ የሀበሻ ገዥዎች ሞክረውታል። መዘዙ ውድቀት ነው የሆነው።
አብይ አህመድ ውትድርናን እናውቅበታለን አይነት ትዕቢትና ድንፋታም ይቃጣዋል። ዳሩ ኮሎኔል አብይ የት ወታደራዊ ተቋም የስታፍ ስልጠና ገብቶ መኮንን እንደሆነ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላየንም። ወዳጄ ደርግ አንቱ የተባሉ ዘመናዊ ወታደራዊ መሪዎችና በጥብቅ ዲሲፕሊን የታነፁ ወታደሮች ነበሩት። በተለይ ከመንገጫገጩ በፊት። ነገር ግን ከመሸነፍ አልዳነም።

ሰሞኑን የትግራይ ክልል ብዙ ሺህ ሚሊሺያዎችን ማስመረቁን ተከትሎ ደግሞ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። እኔ ግን ለምንድነው ለትግራይ ሲሆን ጥያቄ የሚነሳው እላለሁ። ሎጂካሊ እንጠይቅ። አሳምነው ጽጌ (አማራ ክልል) 28000 ሚሊሺያ ሲያስመርቅ ለምን ብለን ጠይቀናል? ኦሮሚያ ክልል በቀደምለት 10000 ፖሊስ (ሚሊሺያ) ሲያስመርቅ ጠይቀናል? በመሠረቱ ሁሉም ክልል የሚሊተሪ ግንባታ ለምን? ተብሎ መጠየቅ አለበት እንጂ ትግራይ ሲሆን ብቻ ጣት መቀሰር አያስፈልግም። አብይ አህመድስ የ4 ቢሊዮን ዩሮ የጦር መሳሪያ ግዥ ሲያካሄድ በፓርላማ አወያይቶ አስፀድቋል? መጠየቅ አለበት።

ልዩ ፖሊስ የሚባል ገዳይ ቡድን በየክልሉ የሚሰለጥነውስ ለምንድነው? ሚሊሺያስ ምንድነው ተግባሩ? መጠየቅ አለበት።
እስከምናውቀው ድረስ ልዩ ፖሊስና ሚሊሺያ አሸባሪ ኃይል ነው። የመንግስት ገዳይ ስኳድ ነው። የደርግ አብዮት ጥበቃ ውርስ ነው።
ለማጠቃለል፣ በዚህ ሀገሪቱ በልዩ ልዩ ችግር በተተበተበችበት ሰዓት ሚሊተሪ ብልድአፕ፣ ወታደራዊ ፓሬድ፣ ጦርነት ጦርነት የሚሸት ወሬ አያስፈልገንም፤ ፖለቲካውን ማስከንና ከአብይ ቅዠት ባሻገር ማሰብ ያስፈልጋል ባይ ነኝ።

መልካም !!

By Tullu Liban