ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ በመብራት ማጣትና መቆራረጥ መክሰሩንና ሊዘጋ

ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ በመብራት ማጣትና መቆራረጥ መክሰሩንና ሊዘጋ እንደሚችል አስታወቀ

ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ

(ena) –ሙገር ነሃሴ 7/200ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ በኤሌክትሪክ ኃይል ማጣትና መቆራረጥ መክሰሩንና ሊዘጋ የሚችልበት ሁኔታ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አካሉ ገብረህይወት ለኢዜአ እንደተናገሩት ሙገር ያለው ዋናው የሲሚንቶ ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሚደርስበት ጉዳት ምክንያት ካለው አቅም ከግማሽ በታች እያመረተ ነው፡፡

በታጠቅ ፋብሪካው ደግሞ በዚሁ በኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦትና መቆራረጥ ምክንያት በአንድ ወፍጮ ብቻ የሚሰራ በመሆኑ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እየከሰረ ይገኛል ፡፡

ለሙገር ከተዘረጋው መስመር ለአካባቢው ነዋሪዎች በመሰጠቱና የነዋሪዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥና ሲመጣ በሚከሰት መቆራረጥና ያልተመጣጠነ ኃይል ወደ ፋብሪካው መግባት ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸውም ነው ኢንጂነር አካሉ የተናገሩት፡፡

የኢንተርፕራይዙ የኢንጂነሪንግ ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ ኢንጂነር አብደና መኮንን እንደገለጹት በተለይ የፋብሪካው የአንዳንድ ዕቃዎች መለዋወጫ በቀላሉ የማይገኝ በመሆኑ ረጅም ጊዜ ለመቆም ይገደዳል፡፡

ከሁለት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የፋብሪካውን ጥሬ ዕቃ የሚያቀርበው ኮንቬየርም እንዲሁ በኤሌክትሪክ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት ፋብሪካው ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ከግማሽ በታች በሆነ አቅሙ ሲሰራ እንደነበር የገለፁት ደግሞ የኢንተርፕራይዙ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ማምረቻ መሳሪያ ጥገና ቡድን መሪ ኢንጂነር ግርማ ባጫ ናቸው፡፡

የክሊንከር ምርት ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ ኢንጂነር አበራ ነጋሽ በበኩላቸው በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራጥ ምክንያት ማቃጠያ መሳሪያው ላይ  ጉዳት  እንደሚፈጠር ጠቅሰው ለዚህ መሳሪያ አነስተኛ ጥገና ለማድረግ ማሽኑ እስኪቀዘቅዝ ድረስ ሦስት ቀን እንደሚያስጠብቅ ይናገራሉ፡፡   ጠግኖም ሥራ ለማስጀመር ደግሞ ከ12 እስከ 18 ሰዓት ሊፈጅ እንደሚችል ነው የሚጠቁሙት፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አካሉ ታጠቅ የሚገኘው የድርጅቱ የሲሚንቶ መፍጫና ማሸጊያ ፋብሪካ “ከተመሰረተበት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን በኤክትሪክ እጦት በግማሽ አቅሙ እየሰራ ነው” ብለዋል፡፡

የፋብሪካው ሦስተኛ የምርት መስመር አካል የሆነው የታጠቅ ፋብሪካ ሲመሰረት እያንዳንዳቸው አራት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልየሚፈልጉ ሁለት ወፍጮዎች ሲኖሩት የተሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ግን ከአንድ ወፍጮ በላይ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ምክንያት ፋብሪካው የተገነባበትን የብድር ገንዘብ እንኳን መክፈል  አልቻለም፡፡

የታጠቅ ፕላንት የጥገና ቡድን መሪ ኢንጂነር ዳንኤል አጥላው እንደሚሉት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት የተጨማሪ ክፍያ ጥያቄዎችን ከማቅረብ የዘለለ አገልግሎት አልሰጣቸውም፡፡

ወፍጮዎቹ በዓመት ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ሊፈጩ የሚችሉ ቢሆንም እስካሁን በግማሽ አቅም ብቻ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው አንደኛው ወፍጮ ባለመስራቱ ብቻ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠር እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋናሥራ አስኪያጅ፤ ችግሩን ለመፍታት በድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሳይቀር ፓርላማውም እንዲያውቀው የተደረገ ቢሆንም መፍትሄ ባለመገኘቱ የሚመለከታቸው ሁሉ መስሪያ ቤቱን ከመዘጋት እንዲታደጉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኢንተርፕራይዙ የታጠቅ ፕላንት ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ የጀመረውን መስመር የመዘርጋት ሂደት በተለይም በተለያዩ ቦታዎች የተተከሉ ፖሎች ባሉበት መቆማቸውንና የኤሌክትሪክ መስመሮቹም ተበጣጥሰው በየሜዳው መቅረታቸውን ኢዜአ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምላሽ እንዲሰጥ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡