መከላከያ ከባድ የጦር መሳሪያዎቹን ከዛላምበሳ ድንበር ማንቀሳቀስ አልቻለም

መከላከያ ከባድ የጦር መሳሪያዎቹን ከዛላምበሳ ድንበር ማንቀሳቀስ አልቻለም

(bbc)—ትናንት ሰኞ አመሻሽ ላይ ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር አከባቢ ከባድ የጦር መሳርያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የመከላከያ ሠራዊት መኪኖች በአካባቢው ባሉ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል።

የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነትን ተከትሎ በአካባቢው ለዓመታት ተሰማርተው የነበሩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ጭነው ሊንቀሳቀሱ ነው የተባሉትን ከሃያ በላይ የሚሆኑ የመከላከያ ከባድ የጭነት መኪኖች ፋጺ በተባለ ከዛላምበሳ ጥቂት ራቅ ብሎ የሚገኘው ስፍራ ላይ የአካባቢው ህዝብ መንገድ ዘግቶ ለቀው እንዳይወጡ መከልከሉን ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

• ካለፈቃድ በዛላምበሳ ድንበር በኩል ማለፍ ተከለከለ

• የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ስለመዘጋቱ መረጃ የለኝም፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

በድንበር አካባቢ ያሉት ሰዎች ይህንን የሠራዊቱን ከባድ የጦር መሳሪያ የማንቀሳቀስ እርምጃን ያስተጓጎለው መስከረም ወር ላይ የተከፈተው የዛላምበሳና የራማ አገናኝ የድንበር መተላለፊያዎች ላይ የኤርትራ መንግሥት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ቁጥጥር ማድረግ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ስጋት ምክንያት እንደሆነ ምንጮች ይገልፃሉ።

በትግራይ ክልል መንግሥት የግሎ መኸዳ ወረዳ የፀጥታ ሃላፊ አቶ ግርማይ ሓዱሽ በድንበር አቅራቢያ የተፈጠረው ይህ ክስተት እውነት መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ ሠራዊቱ በአካባቢው የነበረውን ከባድ መሳሪያዎች ማንቀሳቀሱ በተመለከተ “ህዝቡ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል” ብለዋል።

አቶ ግርማይ ሓዱሽ ጨምረውም በአንዳንድ የድንበር አካባቢዎች ቀደም ሲል ተከፍተው የነበሩ መተላለፊያዎች ሰሞኑን ከመዘጋታቸው ጋር በተያያዘ ህዝቡ በተጀመረው የእርቅ ሂደት ላይ ጥርጣሬና ስጋት እንደተፈጠረ ተናግረዋል።

• የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ?

• መስመር ያልያዘው የኢትዮ-ኤርትራ የንግድ ግንኙነት ወዴት ያመራል?

“ድንበር ላይ ጥበቃ ተቀመንጦ መንገድ እየተዘጋ ባሉበት በአሁኑ ሁኔታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወዴት ነው የሚንቀሳቀሰው? ከነበረበት ቦታ እንዲነሳ እየተደረገ ያለበት ምክንያትም ግልፅ አይደለም? የሚሉ ጥያቄዎች ህዝቡ እያነሳ ነው” ብለዋል አቶ ግርማይ።

ይህንን ክስተት ተከትሎም የመከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው ሊያንቀሳቅሳቸው የነበሩ ከባድ ተሽከርካሪዎቹን እንዳቆመና ዛሬ ከህዝቡ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዞ ማደሩንም ጨምረው ተናግረዋል።

በተመሳሳይም ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በኢሮብ ወረዳ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው የተንቀሳቀሰ ሲሆን ከአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ መሰል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ምንጮች አክለው ይናገራሉ።

በአካባቢው “ከባድ የጦር መሳርያ የሚጭኑ መኪኖች ሲያልፉ ህዝቡ ‘ማብራርያ እንፈልጋለን’ የሚል ጥያቄ አቀረበ እንጂ ወደ ሌላ ግጭት አልገባም” ሲሉ የፀጥታ ሐላፊው ምንም አይነት ችግር አለመፈጠሩን አረጋግጠዋል።

• “አሁን ያገኘነው ሰላም ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው”- ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

• ኢትዮጵያና ኤርትራ፦ ከእራት በኋላ ምን ተወራ?

ከዚህ ክስተት በኋላም ትናንት ምንም አይነት ከባድ የጦር መሳርያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው እንዳልተንቀሳቀሱ ጨምረው ገልፀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የሠራዊቱን እንቅስቃሴን በተመለከተ “ህብረተሰቡ ለተፈጠረው ስጋት ምላሽ ካገኘ፤ መከላከያ ሠራዊት ለምን ተንቀሳቀሰ ብሎ ጥያቄ የሚያቀርብበት ምክንያት አይኖርም” ብለዋል አቶ ግርማይ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት መካከል የተከናወነውን የሠላም ስምምነትን ተከትሎ ከአከባቢው መንቀሳቀስ እንደጀመረ ቀደም ሲል ተዘግቧል።

ይሁን እንጂ ከባለፈው ሳምንት ተጀምሮ ሁለቱን ሃገራት የሚያገናኙ የድንበር መተላለፊያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከተጀመረ በኋላ በሁለቱም በኩል የነበረው እንቅስቃሴ እንደተገታ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይህንን በተመለከተም ከኤርትራም ሆነ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኩል በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ማብራሪያ ለማግኘት አልተቻለም።


“ይሄ ለዉጥ የኛ ነው፡ የራሳችን ነው፡ ተሰዉተነብታል።” የኦሮሞ ነፃነት ግንባር


“የኦሮሞ የነፃነት ትግል ወራሾች ኦሮሞን ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕከል የመለሱት እነ አቶ #ለማ እና ጠ/ሚ #አቢይ ናቸው እንጂ ውጭ ተሰዶ የነበረው ፖለቲከኛ አይደለም።” …
“ከዚህ በኋላ የምንጥለው ጨቋኝ ስርዓት የለም። ኦሮሞ አሁን የሚፈልገው በመሳሪያ የሚያታገለው ሳይሆን ሀገር የሚገነባ አስተሳሰብ በመያዝ በአስተሳሰብ የሚያታገለው ነው። ነገር ግን አሁን ያለውን ክፍተት ተጠቅሞ #ህወሀት_ሊጋልበው የሚፈልግ ግሩፕ እንዳለ ነው የምረዳው።”
ብርሀነ መስቀል አበበ (ዶ/ር)