መንግስት ኦፌኮና ኦነግን ከምርጫው ገፍቶ ለማውጣት በርካታ እጩዎቻቸው ወደ እስር ቤት እንዲጋዙ አደረገ።

መንግስት ኦፌኮና ኦነግን ከምርጫው ገፍቶ ለማውጣት በርካታ እጩዎቻቸው ወደ እስር ቤት እንዲጋዙ አደረገ። ምርጫ ቦርድ ደግሞ እነዚህ እጩዎች
መመዝገብ አይችሉም የሚል በየትኛውም ህግ ላይ የሌለ ትእዛዝ በማስተላለፍ ለብልጽግና ነውረኛ ትብብር አደረገ።
 
አንድ ውይይት ላይ በቴ ኡርጌሳ የታሰሩ እጩዎቻችን እንዲመዘገቡልን ይደረግ ብሎ የቦርዱን ሊቀ መንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ሲጠይቅ ፈፅሞ እንደማይቻል ነግረውታል። በዚህና በሌሎች ጫናዎች ምክንያት ሁለቱ ፓርቲዎች ከውድድሩ ተገደው ወጡ።
 
ጠ/ሚ አብይ በራሱ ፍላጎት handpick ያደረጋቸው የቦርዱ ሊቀመንበር ለገዢው ፓርቲ የተወሰነ መለሳለስ ያሳያሉ የሚል ስጋት የነበረን ቢሆንም እንዲህ ባፈጠጠ መልኩ የገዢው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ ይሆናሉ የሚል ግምት አልነበረንም። በዋናነት ለኦፌኮና ኦነግ የታሰበው ሽረባ የባልደራስ አራት እጬዎችን የሚነካ ሆነና የወ/ት ብርቱካን የብልጽግና-ኢዜማ ወገንተኝነት መጨረሻ ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ ገሃድ ወጣ።
የሚገርመው ነገር ብርቱካን በድጋሜ የታሰሩ ጊዜ የፓርቲ አጋሮቻቸው ባጠቃላይ ሲሉ የነበረው ኢህአዴግ ያሰራቸው በ2002ቱ ምርጫ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ነው የሚል ነበር። ይህ በደል በግል የደረሰባቸው ወ/ት ብርቱካን ግን ዛሬም ሌሎች ላይ ተመሳሳይ ተግባር ሲፈጸም የዳር ተመልካች ከመሆን አልፈው ባልተፃፈ ህግ እጩዎችን በማገድ የብልጥግና ተባባሪ ሆነዋል። በተለምዶ ምጥ ይረሳል ይባላል። በደልም ይረሳል መሰለኝ።
 
ሊቀመንበር ብርቱካን በእስር ላይ እያሉ ካዘኑባቸው ቀናት አንዱ አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ያረፈበት ቀን ነበር። Solitary confinement ላይ ስለነበሩ ሃዘናቸውን እንኳን የሚያጋሩት ሰው አልነበረም። እርግጥ ነው እነደዚህ አይነት የሀገር ዋርካ ሲያርፍ መሸኘቱ እንኳን ባይቻል ሀዘንን የሚያጋሩት ሰው ማጣት ልብ ይሰብራል። በወቅቱ ከወዳጆቼ ጋር ጥሌን ለመሸኘት ሄደን አብዮት አደባባይ በስታምፒድ ልናልቅ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህን ጉዳይ ያነሳሁት ወ/ት ብርቱካን ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ ስለሆነ ነው። ባለፈው አመት እነ ጃዋርም ተይዘው እስር ቤት ሲወረወሩ ጀግና ወዳጃቸው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን የመሰናበት እድል እንኳን አልተሰጣቸውም። ለአንድ ቀን እንኳን ተቀምጠው ለማዘን ጊዜ አላገኙም። ብልጥግና ነውረኛ በሆነ ሁኔታ ከምርጫው እነሱን ገለል ለማድረግ በዚህ መልክ ያሰራቸውን ሰዎች ነው እንግዲህ ወ/ት ብርቱካንም ለምርጫ እንዲመዘገቡ አልፈቅድም ያሉት። የፖለቲካ አቋም ልዩነት እንኳን ቢኖር በራስ ላይ የደረሰ በደል በሌላ ላይ ሲደርስ ተባባሪ መሆን አይከብድም? ያውም ባልተፃፈ ህግ። ህሊና ከወዴት አለህ ያስብላል።
 
ለማንኛውም ሊቀ መንበሯ ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እኩልነት መታገል “ዘረኝነት” ነው ብሎ ከሚያምነው የፖለቲካ ካምፕ የወጡ ስለሆኑ ውሳኔያቸው ብዙም ሊገርመን አይገባም። ብርቱካን ሚደቅሳን አብይ አህመድን ታምራት ነገራን አስቴር በዳኔን ፍቅሬ ቶለሳን ኤርሚያስ ለገሰና የመሳሰሉትን መቀየም ከራሱ ጥላ በመሸሽ ላይ ያለን ሰው እንደመቀየም ነው። ዛሬ ኦሮሞ የተባለ ተቃዋሚ ባጠቃላይ ከምርጫው እንዲወጣ ተደርጎ የአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ በ”ጥሩ ኢትዮጵያዊ” ካባ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ጨርሰዋል። ከዚህ የከፋ ሀገር አፍራሽ መንገድ የለም። ለሀምሳ ሚሊዮን ህዝብ አንድ ፓርቲ ብቻ ቀርቦ ምርጫ የሚል ቀልድ አይሰራም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በቋሚነት የዳር ተመልካች ሆኖ የሚቀጥል ህዝብ አይኖርም። ያኔ ይለይለታል።