“መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ያስገባል”ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

“መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ያስገባል”ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

(bbc)–በትናንትናው ዕለት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር አድርገዋል። ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው በ2012 ዓ.ም በሠላም፣ በፍትሕ ማሻሻያ ሥርዓቶች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎችን ዘርዝረዋል።

በንግግራቸው ወቅትም መንግሥት ባለፈው ዓመት 2011 ዓ.ም በፖለቲካ፣ በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ ሥርዓትና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነበረውን ሀገራዊ ጉድለት ማስተካከል የጀመረበት መሆኑን አንስተዋል።

• እንቅስቃሴ አልባዋ ምጽዋ

ምጣኔ ኃብት

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረግ የዚህ ዓመት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ፣ ዋና ዓላማውም የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት መጠበቅ፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግና ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልፀው “የተጀመረው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና የማፈላለግ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል” ብለዋል።

በዚህ ዓመትም የተመረጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይንም በሙሉ ወደግል የማዘዋወሩ እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን የመተግበሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

• ለ21 ዓመታት የኢትዮጵያን ቅርስ ደብቀው ያቆዩት ኢትዮጵያዊ

የቴሌኮም ሴክተር እንዲሁም በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኙ የተወሰኑ ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት በከፊል ወይንም በሙሉ ወደ ግል ይዛወራሉ ሲሉም አክለዋል።

የዋጋ ንረት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህበረተሰብ ክፍሎች በተለይ እንደሚጎዳ የገለፁት ፕሬዝዳንቷ፣ መንግስት የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ በማስገባት የዋጋ ንረቱ ሸማቾችን እንዳይጎዳ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ሲሉ ቃል ገብተዋል።

የዜጎች መፈናቀልና ግጭት

ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ በኃገሪቷ ውስጥ ግጭትና መፈናቀል የሰፈነበት፤ ውስጣዊ መረጋጋት ኃገሪቷን የፈተነበት ጊዜ መሆኑን አስታውሰው “ግጭቶቹን ተከትሎ የመጣው የውስጥ መፈናቀልም በታሪካችን ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ምዕራፍ ሆኗል” ብሏል።

ምንም እንኳን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የሌላ ኃገራት ዜጎች መጠለያ ብትሆንም “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በገዛ ሀገራቸው ተፈናቃይ የሆኑበትን አሳዛኝ የታሪክ ገጽ አልፈናል።” ብለዋል።

ሠላምና መረጋጋትን ማረጋገጥን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ በርከት ያለ ስራ መሰራቱን ያስታወሱት ርዕሰ ብሔሯ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባለፈው አንድ ዓመት በጋራ ባደረጉት ርብርብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የነበረው የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከመቶ ሺ የማይዘል ሆኗል ብለዋል።

በ2012 ዓ.ም በመልሶ ማስፈርና ዘላቂ ማቋቋም መርሐ ግብር ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ወደተሟላ መደበኛና የተረጋጋ ኑሮ የመመለስ ተግባር በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም የደኅንነት ተቋማት ችግሮች ከመከሠታቸው በፊት ቀድመው “የማነፍነፍ ዐቅማቸው” እንዲያድግና ችግር ሲከሠትም በአጭር ጊዜ የማስቆም ብቃታቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራት ይሠራሉ ብለዋል።

በዚህ ረገድ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊሶችና፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አቅማቸውን የሚያጠናክር ሥራ ይሰራሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ምርጫ

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በ2012 የሚከናወነው ሀገራዊ ምርጫ ሦስት ዕሴቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም ምርጫው በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ግድፈቶችን በሚያርም መልክ እንዲከናወን፣ ነጻና ዲሞክራያዊ ፤ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆንና የፖለቲካ ልሂቃንንና የምልዐተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።

• በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ረቂቅ ጥፋተኛና አቃቤ ህግ ይደራደራሉ

አክለውም መንግሥት የምርጫውን ሂደት ለማሰናከልና ለማጠልሸት የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ተግባራትን በሕግና በሥርዓት የሚያስተካክል ይሆናል ብለዋል።

ከሀገራዊ ምርጫው ባሻገር የሚከናወኑ የሕዝበ ውሳኔ ሂደቶችም ምርጫውን በተመለከተ በተቀመጡት ሦስቱ ዕሴቶች መሠረት የሚከናወኑ ይሆናሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።

የፍትሕ ሥርዓቱ ማሻሻያዎች

የፍርድ ቤት ማሻሻያዎችን ለማከናወን የሦስት ዓመታት መርሐ ግብር ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቷ፣ በዚህም መሠረት በሦስት ዘርፎች የሚከናወን የፌዴራል ፍርድ ቤቶችና የዳኝነት ማሻሻያ ዕቅድ ተቀርጿል ብለዋል።

የዳኝነት ነጻነትን፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ማጠናከር፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ማስፋትና የሕግ ዕውቀት እንዲዳብር ማድረግ፣ እንዲሁም የዳኝነትን ውጤታማነትና ቅልጥፍና ማሻሻል የማሻሻያው ዋና ዋና ትኩረቶች መሆናቸውንም አስቀምጠዋል።

ውጤታማ እና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር በተያዘው ዕቅድ ደግሞ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አደረጃጀትና ሥልጣን የሚወስኑ ዓዋጆችን ማሻሻያ የማጠናቀቅ፤ የየአዋጁን ማሻሻያ ተከትሎ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን የተሻለ ለማድረግ አስፈላጊ አደረጃጀትን የመዘርጋትና ደንቦቹን ማውጣት ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል ፕሬዝዳንቷ።

ሕዝቡ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚያቀርበውን ከፍተኛ የአገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ የሚያሥችል፤ በዓመት እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ (250,000) መዛግብት ለማስተናገድ የሚያስችል አወቃቀር መፍጠር መታሰቡንም ገልፀዋል።

• “ቤተ መንግሥቱን ለማስዋብ ለሙያችን የሚከፈለን ገንዘብ የለም” መስከረም አሰግድ

አክለውም የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መምሪያ፣ የቁጥጥርና ክትትል ክፍሎችን በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋም እና ማደራጀት፤ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር፤ የዳኝነት አገልግሎት ሥራ ደጋፊ የሆኑትን የአስተዳዳር አካላት ውጤታማነት ማረጋገጥ ዋነኞቹ ትኩረቶቹ ናቸው ብለዋል።

የውጪ ግንኙነት

በ2011 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ ሀገራት በእስር እና በእንግልት ላይ የነበሩ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሱት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሥራ ሥምሪት ስምምነቶችን መደራደርና ከተወሰኑት ጋር ስምምነትን ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል።

ከጎረቤት ሀገራትና ከሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ጋር ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ጥምረት ለመፍጠር የሚያግዙ የነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቶች እና ያለ ቪዛ ወደ ሀገር ውስጥ መግባትን የመፍቀድ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

• በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የደረሱት ሥምምነት ምንድን ነው?

“የውጭ ግንኙነት መርሃችን ፉክክርንና ትብብርን ባማከለ መልኩ እንዲከናወን ታስቧል” ያሉት ፕሬዝዳንቷ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን አሸናፊ ሆኖ መውጣትም ያስፈልጋል በማለት፣” ለዚህ ደግሞ የውጭ ግንኙነታችን በውስጥ ጥንካሬያችን ላይ ይወሰናል፡፡ ጠንካራ አንድነት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓትና ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ሲኖረን የውጭ ግንኙነታችንም በዚያው ልክ ጠንካራ ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፍ መስኮች ተፎካካሪ ኃይል ሆነን ለመውጣትም እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።