መንግሥታዊ ሕገ-ወጥነትና ሥርዓተ-አልበኝነትም ይቁም–በአስቸኳይ!

መንግሥታዊ ሕገ-ወጥነትና ሥርዓተ-አልበኝነትም ይቁም–በአስቸኳይ!

(batipost)—-ሥርዓተ-አልበኝነትና ሕገ-ወጥነት፣ ሁል ጊዜም በሁሉም ቦታ፣ እኩል፣ ሊኮነኑ ይገባል። ሕዝብ፣ ለወራት (እና ለዓመታት) በሕገ-ወጥ ታጣቂዎች ሲወረር፥ በመቶ ሺህዎች ሲፈናቀል፥ ሲሰደድ፥ በተዘጋ ቤት ከነልጆቹ በእሳት ሲቃጠል፥ ሲታረድና ሲገደል አንድም ቀን ጥፋቱን ሳንኮንን፥ ጥፋተኞቹን ለፍትህ ሳናቀርብ፥ ተበዳዮቹን ሳንጠይቅና አስፈላጊውን እርዳታና ጥበቃ ሳናደርግላቸው መቆየትም አግባብ አይደለም፤ ወደፊትም ያስጠይቃል።

እስከዛሬም ድረስ፣ በምሥራቅና በደቡብ-ምሥራቅ ኦሮምያ፥ በወሎ፥ ወዘተ እየቀጠለ እንዳለው ዓይነት የሽብርና የጦርነት ተግባር፣ የአንድን አካባቢ ዘላቂ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባ መጠነ-ሰፊ ሕገ-ወጥነት ያለ መከልከል ሲፈፀም፣ የመንግሥት ሕግ አስከባሪዎች፥ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የአገር መከላከያ ሠራዊት አካላት ችግሩን እያዩ እንዳላዩ አልፈዋል።

ባለሥልጣናት፣ ስለችግሩ መኖር ለመናገር እንኳን ድፍረት ያጡ እስኪመስል ድረስ ዝምታን መርጠዋል። የሕዝቡን የድረሱልን ጥሪ ካለመስማት አልፎም ምንም ችግር የሌለ በሚመስል ደረጃ “የፍቅርና የይቅርታ” ስብከትና ጉዞ (“ሽርሽር”) ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። ለሕገ-ወጥነትና ሥርዓተ-አልበኝነት ምላሹ ባዶ የፍቅርና የይቅርታ ስብከት መሆን አልነበረበትም።

በየቀኑ በበርካታ ቁጥር እያለቀ፥ ከቀየው እየተነቀለና ከመጥፋት አደጋ ጋር ፊት ለፊት ለተፋጠጠ ሕዝብ “እንደመር” የሚል ባዶ መፈክር አይፈይደውም፤ እንዲያውም ቢደጋገምም አይሰማውም። መኖር ከፍቅር፣ ሕይወት ከ”መደመር”፥ ሰላም ከይቅርታ ይቀድማልና።

መንግሥት፣ ለረጅም ጊዜ ሕገ-ወጥነትን ባለ መቆጣጠር፣ ሲሻውም ግልፅ የሆኑ ሕገወጥ ተግባራትን ያለገደብ በመፈፀም፣ ለሕገ-ወጥነት መንሰራፋት ትልቁንና ዋንኛውን አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቶአል። መንግሥት ለአሰራሩ ሥርዓትን፣ ለንግግሩም ተቋማትን ባለማበጀት፥ ሥርዓተ-አልበኝነት እንዲስፋፋ (ሳያውቀውም ቢሆን) ሲያበረታታ ቆይቷል።

ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን ኢሰብአዊና ጭካኔ የተሞላበት (brutal) ግድያዎች ቸል በማለት፣ ማህበረሰቡ በህግና በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዳይኖረው፣ የነበረውም ትንሽ እምነት እንዲመናመን፣ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። የግፍ ብዛት የወለደው ተስፋ-ማጣትም ተከትሏል።

በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በዳይን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር መሳሳቱ (በብዙ አካባቢዎች ከናካቴውም አለመኖሩ) ተበዳዮች ፍትህን በግላቸው እንዲፈልጉ (“ህግን በእጃቸው” እንዲያስገቡ) አስገድዶአል።

ዛሬ ዛሬ፣ ጭካኔ የተሞላበት፥ የከራረመ፥ መንግሥታዊ የኃይል ተግባርና መጠን-የለሽ የጎንዮሽ አውሬነት (horizontal brutality)፣ ጨካኝ ግለሰቦችን ፈጥሮአል። (በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች የታዩት የጎንዮሽ ጭካኔዎች (horizontal brutalities) መዋቅራዊ ሥር ካለው መንግሥታዊ ጭካኔ የመነጩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።)

ለዘመናት ፖለቲካዊና መንግሥታዊ ጭካኔን ስንቃምወም የኖርነው፣ (“ማዕከላዊና ተመሳሳይ የማሰቃያ ማዕከሎች ይፍረሱ!” ስንል የነበረው)፣ ውሎ አድሮ እንደዚህ ዓይነት የጎንዮሽ ጭካኔ እንዳይበራከት ለማስጠንቀቅም ነበር።

ፖለቲካዊ ጭካኔ ማህበራዊ ሥነ-ምግባራዊ ድሩን (ማለትም የሕብረተ-ሰቡን moral fabric) ሸርሽሮ ማህበራዊ ጭካኔን እንዳይወልድ፣ ፖለቲካዊ የኃይል ተግባርም (political violence) ማህበራዊ የኃይል ተግባርን እንዳያስከትልና እንዳያባብስ ተብሎ ነበር።

ፖለቲካዊ የኃይል ተግባርን በመኮነን “ፈፃሚዎቹን በሕግ አግባብ ተጠያቂ አድርጉ!” ስንል የነበረውም መንግሥታዊ ጭካኔን በመርገም፣ ማህበረሰባዊ ነውር እንዲሆን ለማስልቻ ነበር። መንግሥታዊ ጭካኔ ግለሰብንና ማህበረሰብን ጨካኝ ያደርጋልና። (State brutality–or its complicit indifference–brutalizes society and the individuals thereof.)

ለረጅም ጊዜ “ተቋማዊነት የጎደለው፥ መርህ-የጎደለው፥ የሕግ መሠረት ያልያዘ አሰራርና ንግግርን ተዉ!” ተብለው ሲመከሩ አልሰማ ያሉ መሪዎቻችን፣ “በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል አስቁሙ! በዳዮችንም ተጠያቂ እንዲሆኑ ለፍርድ አቅርቡ!” ሲባሉ (በይቅርታና መደመር ሥም) አሻፈረኝ ያሉ መሪዎቻችን፣ ዛሬ ደርሰው ሕዝብን (ያውም እየመረጡ) በሥርዓተ-አልበኝነትና በሕገ-ወጥነት መኮነናቸው ያስገርማል፥ ያሳዝናል፥ያስቆጣል።

ለወትሮውም ቢሆን፣ በመከላከያ ሠራዊት ሲታመስ ለኖረና ከዚህም የተነሳ ለተሰቃየ አገር፣ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተደገፈ ፍትህና ሥርዓት ማስፈን የሚቻል ይመስል፣ ሠራዊት ፊት ቆሞ ህዝብን “ሕገ-ወጥና ሥርዓተ-አልበኛ መንጋ” ብሎ ማለት ደጋፊ መንጋ ለማብዛትና እነዚህኑ ለማስደሰት ብቻ ብሎ የተበደለውን ሕዝብ እንደመስደብ ነው።

ሕጋዊነትና የሕግ የበላይነት ሥርዓት (rule of law) መሠረቱም፣ ግቡም፣ ሁሉን ጥፋት በእኩል ደረጃ፥ ሁሉን አጥፊ በእኩል ዓይን፣ በማየት መፍረድ ነው።

መንግሥታዊ ሕገ-ወጥነትን፥ ፖለቲካዊ ሥርዓተ-አልበኝነትን፥ እና መዋቅራዊ የጭካኔ ተግባርን ሳታስቆም፣ ሕጋዊነትን መጠበቅ፥ የሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓትን ከተወሰነ የሕዝብ ክፍል መጠየቅ፥ እና አንዳንድ የጎንዮሽ ጭካኔዎችን እየመረጡ መኮነን ግብዝነት ነው። መፍትሄም አይሆንም።

አሁንም እንላለን፦

1. ሕገ-ወጥነት ይቁምልን። መንግሥታዊ ህገ-ወጥነትም ይቁምልን። መግሥታዊ ሥርዓተ-አልበኝነት ይቁምልን። ለምሳሌ፦ የልዩ ኃይል ወረራ (እና የመከላከያ ክፍሎች ለዚህ ኃይል የሚሰጡት ድጋፍ) ይቁም። ልዩ ኃይል በይፋ ይፍረስ። ጥፋተኞች በሕግ አግባብ ይጠየቁ።

2. የሕግ አስከባሪ ኃይሎች፣ የፖለቲካ ወገንተኝነትን ተመርኩዘው ከመስራት ይታቀቡ። የእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት፥ ደህንነት፥ ንብረትና ሰብዓዊ ክብር እኩል ዋጋ የሚሰጠው ከሆነ በዚሁ ልክ እኩል ጥበቃ፥ እኩል እንክብካቤ፥ እኩል ርህራሄና እኩል ዋስትና ሊሰጠዉ ይገባል። አንድ አካባቢ ያለ ዜጋ ሲጎዳ አለሁ-ባይነትን ማሳየትና የሌላው አከባቢ እልፍ አእላፍ ዜጎች ሲጎዱ ዝም ማለት፣ የመንግሥትን ወገንተኝነት እንጂ ሕጋዊነትና ሥርዓት ማስፈንን አያሳይም።

 • ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ይቁም!
 • እኩልነት ይከበር!
 • የመንጋ ዘረኝነት፥ ጥላቻና ንቀት ይቁም!
 • አገራዊ ወጥነት ያለው፣ ፍትሃዊ የሕግ ማስከበር ሂደት ይስፈንልን!

3. አጥፊዎችን ከመቅጣት ይልቅ ተጎጂዎችን “መንጋ፥ ሥርዓተ-አልበኛ፥ ወዘተ” እያሉ የተውሶ ሥም መስጠት፣ ለጊዜው የራስን መንጋ ቢያስደስትም ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም። ሥም መለጠፍ (labeling) ይበልጥ ያጨካክናል እንጂ ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም። ሥም መለጠፍና ሕዝብን እየለዩ መስደብ ይቁም።

4. ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን መሻትና መስጠት ያስፈልጋል። አንገብጋቢም ነው። ዛሬ፣ ለፖለቲካዊ ጥያቄዎች በተቻለ መጠን፥ በተቻለ አቅምና በተቻለ ፍጥነት ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የነበረውንና (እስካሁንም ያለውን) ሥርዓት ወደ “ለውጥ እንቅስቃሴ” እንዲገባ ያስገደደውም ችግር ፖለቲካዊ ችግር መሆኑ መረሳት የለበትም። አሁንም የሕዝቡ ጥያቄዎች የማይመለሱ ከሆነ፣ ከበፊቱ የላቀ አለመረጋጋት እንደሚፈጠር ለሚመለከተው ሁሉ ግልፅ ሊሆን ይገባል።

5. የመንግሥት አሰራር ተቋማዊ፥ ሕጋዊ፥ ሕገ-መንግሥታዊ እና በመርሃ-ግብር (program) የሚመራ ይሁንልን። የመሪዎች ንግግር ሕገ-መንግሥታዊ ፥ሕጋዊና ተቋማዊ መሠረትን እንዲይዙ አስፈላጊው ትኩረትና ጥንቃቄ ይደረግ። የመግሥት መሪዎች ንግግሮች፣ ከከፋፋይ ትርክቶችና ከፖለቲካ ወገንተኝትነ የፀዱ ይሁኑልን።

6. በየአጋጣሚው የሕዝብን ሃብትና መሬትን መዝረፍ እየተንሰራፋ ስለሆነ በአስቸኳይ ይቁምልን።

7. ሰላም በሌለበት ሥርዓት ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ጦርነት ይቁምልን። ወገን ለይቶ ማስታጠቅ፥ ወገን ለይቶ ትጥቅ ማስፈታት ይቁምልን። ፍትህ በሌለበት መረጋጋት አይኖርም። ስለዚህ ለፍትህ (ለማህበረሰቦች እውነት፥ ሃቅና፥ የፖለቲካ ብሶት) ትኩረት ይሰጥ።

8. ለዘላቂ ሰላም፥ ለሕጋዊነትና ለሕግ የበላይነት፥ ለማህበረሰባዊ መረጋጋትና ሥርዓት፥ ብሎም የሕዝብን ፖለቲካዊ ተስፋ ለማለምለም–ለዚህ ሁሉ–መሠረቱም፣ መልህቁም፣ ዋስትናውም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሆነ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ በአስቸኳይና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋልና፣ ይሄ የሽግግር ሥራ አሁኑኑ ይጀመርልን።

ብሩክ ሰንበት!

3 Comments

 1. Well pointed out, Dr Ararssa! Ethiopian authorities and Ethiopians must learn from past mistakes and engage in mature politics. Labeling justice seeking citizens and referring to them as “herds”, ” disregulated”, and so on, while turning blind eyes to their yearning for safeguarding of their lives and belongings is quite absurd. The Ethiopian government must be determined and regulate its own security forces and hold abusers to account. Then, the population would show their civility and start to listen to authorities. It is going to be ‘business as usual’ if the administration of Dr Abiy Ahmed resorts to pleasing certain section of the population at the expense of others rather than prescribing justice and safety for all the peoples in that country.

  Patience and wisdom shall prevail!

  OA

  • Dear Tsagaye!
   Your matured ideas, scholarly analysis and glimpse on the current political reality in Oromia echoes what most of us have in mind. You are a voice for many and like a mind reader about what “our own” leaders are doing to our people. I am so sick of the maltreatment by Prime minister Dr. Abiy and President Lamma. We are not asking to be treated better or different but at least fairly equal. Where was the government when tens and hundreds of Oromo people were/are massacred in Esat Oromia and Showa zone? How comes lawlessness just started in Oromia the region that is victim of lawlessness. Did P. Abiy or P. Lemma say anything about the two Oromo brothers who were killed in Wallo zone last week? They were just killed because they were Oromo. The warning to qeerroo “ye manga polotika” is victim blaming. I am sure the prime minister and president Lama may reflect on about the fairness for Oromo people. This is disconcerting. The “manga politics” has brought all the changes we see today in this nation and that many who never labored for are harvesting. Qeerroo shouldn’t be a victim. Please…

   Regards
   Tola

Comments are closed.