ሕዝብ ያፈናቀሉና ያንገላቱ 468 ከክልል እስከ ቀበሌ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ..

ሰበር መረጃ❗️

#Ethiopia : ሕዝብ ያፈናቀሉና ያንገላቱ 468 ከክልል እስከ ቀበሌ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለዋል ፤ 420 ባለስልጣናት እየተፈለጉ ነው።

ባለፉት አመታት ሕዝብ ያፈናቀሉና ያንገላቱ የቀድሞ ሹሞችና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከአለም አቀፉ የፖሊስ ድርጀት ኢንተርፖል ጋር ጭምር በጋራ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ተናገረ፡፡እስካሁን 468 ከክልል የካቢኔ አባላት እስከ ቀበሌ የስራ ሀላፊ ድረስ ያሉበት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው፡፡ከ420 የማያንሱ ተጠርጣሪዎችም ገና በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉ ጠቁመዋል፡፡ክትትሉ ግን ቀጥሏል ተብሏል፡፡

በወንጀሉ ተሳትፈው ከአገር የወጡትንም ጭምር ህግ ፊት ለማቅረብ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሏቸውን የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና የፀጥታ አስከባሪ አባላትን ቁጥር እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡ሚኒስትሯ እንዳሉት በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩ ከተከሰተው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከ108 ተጠርጣሪዎች 85 ያህሉ ተይዘዋል፡፡ከመካከላቸው አንዱ የወረዳ አስተዳዳሪ ሲሆን ሌላ አንድ የፖሊስ ጣቢያ ሀላፊ እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ከዜጎች መፈናቀልና ግጭቶችና ጥቃት ጋር በተያያዘ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 23ቱ ከክልል የካቢኔ አባላት እስከ ሚሊሻ ያሉ የፖለቲካና የፀጥታ አስከባሪ አመራሮች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት የመስሪያ ቤታቸውን የ9 ወር የስራ ክንውን ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አቅርበው ከአባላቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ነው፡፡

ሸካ አካባቢ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 10 የፖለቲካ አመራርና የፀጥታ አስከባሪ አባላት ይገኙበታል ብለዋል፡፡ከጉጂና ጌዲኦ ጋር በነበረው ግጭት ግን 312 ተጠርጣሪዎች ቢለዩም እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት 9 ብቻ ናቸው፡፡ይህም በየደረጃው ያለ የፖለቲካ አመራር ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልሆነ ነው ብለዋል፡፡እስካሁን በትብብር ወንጀለኞችን አሳልፎ እንዲሰጡ ክልሎችን ታግሰናል ያሉት የሰላም ሚኒስትሯ አሁን ግን ይህን ደረጃ አልፈን ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመተባበር ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ስምሪት ተጀምሯል ብለዋል፡፡

Source : የሰላም ሚኒስቴC