”ሃገርን ከጦርነት ታደኩ. . . መሪዋም የኖቤል ሽልማትን አሸነፈ” ትራምፕ

”ሃገርን ከጦርነት ታደኩ. . . መሪዋም የኖቤል ሽልማትን አሸነፈ” ትራምፕ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ምሽት በኦሃይሆ ግዛት ቴሊዶ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ።

(bbcamharic)–ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ምሽት በኦሃይሆ ግዛት ቴሊዶ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በሚያደርጉበት ወቅት፤ ሊቀሰቀስ የነበረ ‘ትልቅ ጦርነት’ ማስቀረታቸውን በዚህም የሃገሪቱ መሪ የኖቤል ሽልማት እንዳሸነፈ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በቅስቀሳ ንግግራቸው ወቅት፤ በሃገራት መካከል ሊከሰት የነበረን ‘ትልቅ ጦርነት’ ማስቆማቸውን እና እርሳቸው ጦርነት እንዳይከሰት በማድረጋቸው የሃገሪቱ መሪ የኖቤል ሽልማትን እንዲያኝ ማስቻላቸውን በመጠቆም፤ እርሳቸው የኖቤል ሽልማትን ያላገኙበትን ምክንያት ለማስረዳት ሞክረዋል።

• “አሸባሪዎችና ጽንፈኞች በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ መሰረት ለመጣል እየጣሩ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

• ዶናልድ ትራምፕ ተከሰሱ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በንግግራቸው ስለ የትኛው ሃገር መሪ ወይም በየትኞቹ ሃገራት መካከል ሊከሰት ስለነበረው ‘ትልቅ ጦርነት’ በቀጥታ ያሉት ነገር ባይኖረም፤ በርካቶች ንግግራቸውን ከኢትዮጵያው መሪ እና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እንዲሁም ከግብጽ እና ኢትዮጵያ ጋር አገናኝተውታል።

ከግብጽ በተጨማሪ ጉዳዩን ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጋር ያያዙትም አሉ።

ትራምፕ ያሉት ምን ነበር?

ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት፤ “ስለ የኖቤል የሰላም ሽልማት ልነግራችሁ እችላለሁ፤ ከስምምነት ደረስኩኝ፤ ሃገር አዳንኩኝ፤ እንደሰማሁት የዚያ ሃገር መሪ ‘ሃገሩን በመታደጉ’ የኖቤል ሽልማት ማግኘቱን ሰማሁ። እኔ በዚህ ላይ ተሳትፎ ነበረኝ? አዎ!። ግን እኛ እውነታውን እስካወቅነው ድረስ ምንም አይደለም። [ጭብጨባ እና ድጋፍ] ትልቅ ጦርነት ነው ያስቀረሁት። ሁለት ሃገሮችን ነው ያዳንኩት” ብለዋል።

በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ትራምፕ የኖቤል ሽልማት ያላገኙበትን ምክንያት ሲያጥላሉ ነበር።

• ትራምፕ፡ “ወጣትና የተማሩ ስደተኞችን እንቀበላለን”

• የዶክተር ዐብይ አሕመድ ፊልም

ጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ሽልማትን ያሸነፉት በዋነኝነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሠላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑን በማስታወስ ትራምፕ ደግሞ በዚህ ላይ የነበራቸው ድርሻ ምንም ነው ያሉ በርካቶች ናቸው።

በሌላ በኩል ሚያዚያ አጋማሽ 2010 አካባቢ አሜሪካዊው አምባሳደር ዶናልድ ያማመቶ ወደ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ያደረጉትን የሥራ ጉብኝት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሠላም እንዲሰፍን የአሜሪካ መንግሥት እና ትራምፕ ሚና ነበራቸው፤ ትራምፕም የሚያወሩት ስለዚሁ ነው የሚሉም አሉ።

ከሁለት ወራት በፊት የግብጽ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ በግደቡ ዙሪያ ከስምምነት ለመድረስ የየሃገራቱ የቴክኒክ ኮሚቴዎች አራት ስብሰባዎችን ለማድረግ፤ ይህ ካልሆነ ከዚህ ቀደም በነበራቸው ስምምነት መሠረት ጉዳዩን ለየሃገራቱ መሪዎች አሊያም አደራዳሪ ለማስገባት በዋሽንግተን ከስምምነት ደርሰው ነበር።

ከስምምነቱ በኋላ ትራምፕ በዋይት ሃውስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹን አግኝተው አነጋግረዋል።

ደስቲን ሚለር የተባለ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በትዊተር ገፁ ላይ “ትራምፕ የግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሚንስትሮች ስብሰባ ላይ አንድ ጊዜ ነው የተገኘው። በግድቡ ዙሪያ ለተካሄዱ እና ለተገኘው ውጤት ባለቤትነቱን ሊወስድ ይፈልጋል እንዴ?” ሲል ጠይቋል

በጉዳዩ ላይ የአሜሪካንን ጣልቃ ገብነት ግብጽ እንጂ ኢትዮጵያ አልፈለገችም በማለት ደስቲን ሚለር የፕሬዝደንቱን ሃሳብ አጣጥሏል።